ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባዔ የተለያዩ አዋጆችን አፀደቀ

ባሕርዳር፤ ታሕሳስ 17/2018(ኢዜአ)፡ - ‎የአማራ ክልል ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባዔ የተሻሻለውን የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን አፀደቀ።

የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ‎አዋጁ በፌዴራል ደረጃ ተሻሽሎ ከፀደቀው ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የወጣ መሆኑም ተመላክቷል።


 

‎‎የክልሉ መሬት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ለምክር ቤቱ እንደገለጹት፤ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጁ የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል ነው።

‎የገጠር መሬት ባለመብቶች መሬታቸውን ማከራየት፣ በዋስትና ማስያዝ፣ ከባለሃብቶች ጋር በጋራ ማልማትና በውርስ ወይም በስጦታ ለማስተላለፍ የሚፈቅድ እንደሆነ አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ ዋስትና በመስጠት ያፈራውን ንብረት የመጠቀም መብትን ለማጠናከርና የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማደራጀት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

‎እንዲሁም የሴቶችና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን የመሬት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አካታች የመሬት አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

‎የምክር ቤቱ የግብርናና አካባቢ ጥበቃና ውሃ ሃብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከፍያለው ሙላቴ በበኩላቸው፤ የአዋጁ መፅደቅ ከመሬት ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ‎ጉባዔ በተጨማሪም የፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ስርዓት ፣ የኤክስሳይዝ ታክስን ለማሻሻል የወጣን አዋጅና የተሻሻለው የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች አዋጆች ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም