ቀጥታ፡

የአመራር ክኅሎትን በማሳደግ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ

ሠመራ፤ ታኅሣስ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በጤናው ዘርፍ የአመራር ክኅሎትን በማሳደግ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።


 

በአፋር ክልል የጤና ሥርዓቱን በዘመናዊ የአሥተዳደር ሥርዓት ለመምራት የሚያስችል ተከታታይና ተግባር ተኮር ሥልጠና የተከታተሉ 80 የጤና ባለሙያዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በሠመራ ተካሂዷል። 
 
በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ሳሀረላ አብዱላሂ እንዳሉት፤ የጤና ባለሙያውን ክኅሎት በሥልጠና ማሳደግ ሚኒስቴሩ በትኩረት ከያዛቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ነው። 
 
በዚህም መሠረት በጤናው ዘርፍ የአመራር ክኅሎትን በማሳደግ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ለማሳለጥ ሚኒስቴሩ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
 
ሚኒስቴሩ የተለያዩ መርሐ-ግብሮችን በመንደፍ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ገልፀው፤ በጤናው ዘርፍ የአመራር ክኅሎት ለማሳደግ እንዲቻል የተሰጠው ሥልጠናም የዚሁ አካል ነው መሆኑን አስታውቀዋል።

ሰልጣኞች ከሥልጠናው የቀሰሙትን ዕውቀት በቀጣይ ሌሎችን በማብቃት ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን ሀቢብ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞች በጤና ተቋማት ውስጥ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ተግባር ተኮር ሥልጠና መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
 
የጤና ባለሙያዎቹ በሥልጠናው በመታገዝ ጠንካራ የጤና ሥርዓትን በመተግበር የተሳለጠ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
 
የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል ባለሙያዎችን ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት አድንቀው፤ ማኅበሩ የበኩሉን ለማገዝ ጥረት ያደርጋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዓለማየሁ መኮንን ናቸው።

ከገዋኔ፣ ጭፍራና ተላላክ ወረዳዎች ከሚገኙ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጽሕፈት ቤቶች የተውጣጡ 80 የጤና ባለሙያዎች ሥልጠናውን መውሰዳቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም