በሀገር ክብርና ጥቅም ቀይ መስመር ሊኖረን ይገባል- ዑስታዝ አቡበከር አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ክብርና ጥቅም ቀይ መስመር ሊኖረን ይገባል- ዑስታዝ አቡበከር አህመድ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ክብርና ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የጋራ አቋም መያዝ እንደሚገባ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ መምህሩ ዑስታዝ አቡበከር አህመድ ገለጹ።
ሀገርን በመግባባትና ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን እንደ ታሪካዊ ዕድል መጠቀም እንደሚገባ አንስተዋል።
የአንድ ሀገር ሕልውና በማህበረሰቡ የአብሮነት፣ የመቻቻልና የጋርዮሽ እሴቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ዕሙን ነው።
ግብረ ገብነትና የማህበረሰብ መስተጋብር መሰረት የሆኑ እሴቶች መሸርሸር ደግሞ የማህበረሰቡን ሰላም ከማናጋት፣ ቅራኔ ከመፍጠር ባሻገር የሀገር ቀጣይነትና ብሔራዊ ጥቅም ሳንካ ይሆናል።
ዕውቁ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ መምህር ዑስታዝ አቡበከር አህመድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያን ማህበራዊ እሴቶችና ህጸጾች፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ ምክክርና ብሄራዊ ጥቅሞችን አስተሳስረው አብራርተዋል።
ሚዲያ ትውልድን ለማነጽና ለሀገር ገጽታ አይተኬ ሚና ቢኖረውም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ልቅ እና ያልተገራ በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ እያመዘነ እንደሆነ ያምናሉ።
ሚዲያ በቅጡ ካልተመራ ከዕድል ይልቅ ስጋቱ ያመዘነ፣ የማህበረሰባዊ መስተጋብር፣ የአብሮነትና የሰላም መሰረት የሆኑ እሴቶችን የሚያናጋ በመሆኑ መስመር ማበጀት እንደሚሻ ገልጸዋል።
ቻይናን መሰል ሀገራት ሀገራዊ እሴቶችን የሚንዱ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ከመቆጣጠር ባሻገር በራሳቸው ቅኝት እንዲመሩ ማድረጋቸውን በማውሳት መንግሥት በዚህ ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚና ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከባህልና ከሃይማኖት ያፈነገጡ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘቶች መበራከት የሃይማኖት ተቋማት በትውልድ ስነ ምግባር ላይ በአግባቡ እንዳልሰሩ ሁነኛ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚስተዋሉ አሉታዊ መልኮች ከየትኛውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ያፈነገጡ መሆናቸውን በመጠቆም፣ የእምነት ተቋማትና ልሂቃን በግልም ሆነ በጋራ ተቋማት በኩል ትውልድ ግንባታ ላይ አበክረው መስራት እንደሚገባቸው ነው ያነሱት።
ሀገር የጋራ ነው ያሉት ዑስታዝ አቡበከር፤ የሀገርን መሰረትና መገለጫዎቿን የሚጻረሩ አካሄዶችን የማረም፣ ትውልድ የመቅረጽ፣ የማነጽና የመገሰጽ ኃላፊነት የሁላችንም ነው ብለዋል።
ከነባር ኢትዮጵያዊ እሴቶች መካከል መረዳዳትን እንደ አብነት አንስተው፤ ማህበራዊ ሚዲያን ለዚህ በጎ እሴት በአግባቡ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ተቋማት እንዳሉ አልሸሸጉም።
በአንጻሩ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ኢ-ስነ ምግባራዊና ኢ-ሃይማኖታዊ የሆኑ ማህበረሰብን የማታለል አካሄዶች በስፋት እንደሚስተዋሉ በማውሳት ተችተዋል።
የጋራችን የሆነች ኢትዮጵያን የጋራ የአብሮነት እሴቶችን ማጎልበት፣ ሲንከባለሉ የቆዩ የልዩነት ትርክቶችን ለማረቅ ደግሞ መወያየትና መመካከርን እንደ ሁነኛ አማራጭ አንስተዋል።
በዚህ ረገድ ሀገራዊ የምክክር ሂደት መጀመሩ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን በማንሳት፤ በምክክር ሂደቱ በመሳተፍ ለስኬታማነቱ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሀገራዊ ጥቅሞችና ጉዳዮች ለግል ጥቅምና ፍላጎት መሸጥ እንደሌለባቸው በማንሳት፤ ከብሔራዊ ጥቅሞች በተቃርኖ መቆም የሀገር ክህደት ነው ብለዋል።
ለሀገር ክብር፣ ጥቅምና ገጽታ ቀይ መስመር ማበጀት እንደሚያሻም ነው ዑስታዝ አቡበከር ያስገነዘቡት።