በነቀምቴ ከተማ ለወጣቶች በተፈጠረ የስራ እድል በርካቶች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ ከተማ ለወጣቶች በተፈጠረ የስራ እድል በርካቶች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው
ነቀምቴ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦በነቀምቴ ከተማ በሌማት ትሩፋት ኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች ለወጣቶች በተፈጠረ የስራ እድል በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የከተማዋ የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
የነቀምቴ ከተማ የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ብርሀኑ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤በበጀት ዓመቱ ለ14 ሺህ 560 የከተማዋ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድል የመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።
በተለይም በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በጨረቃ ጨርቅ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በግብርና እና ሌሎችም ዘርፎች ወጣቶች እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በበጀት ዓመቱ እስካሁን በእነዚህና ሌሎችም ዘርፎች ወጣቶች እየሰሩ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
እየሰሩ በመጠቀምና በመቆጠብ ጭምር የወደፊት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ የሚጥሩ በርካቶች መሆናቸውን አንስተው እስካሁን ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ስለመቆጠባቸው ጠቅሰዋል።
በነቀምቴ ከተማ በሌማት ትሩፋት ኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች ለብዙ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የገለጹት ኃላፊው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች በበኩላቸው፤በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአያና እና ሲምቦ የሽርክና ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ኬና አያና፤ ከሁለት አመት በፊት በተሰማሩበት የጨርቃጨርቅ ምርት ስኬታማ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግሯል።
በድርጅቱ የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ቆንጂት በንቲ፤ በስራው ገቢ ከማግኘት ባለፈ ለቀጣይ ህይወቷ የሚጠቅም እውቀትና ክህሎት እያካበተች መሆኑን ገልፃለች።
በተገኘው የስራ እድል አሁን ላይ ከራሷ አልፋ ቤተሰቦቿን እያገዘች መሆኑንም ተናግራለች።
በአካባቢው እየተፈጠረ ባለው የስራ እድል በርካታ ወጣቶች ወደ ስራ እየገቡና ተጠቃሚ እየሆኑ መሆኑንም ገልጻለች።