የተፈጠረልን የሥራ ዕድል ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር በዘርፉ እውቀት እንድንቀስም እያገዘን ነው- ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጠረልን የሥራ ዕድል ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር በዘርፉ እውቀት እንድንቀስም እያገዘን ነው- ወጣቶች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ በተመረቁበት የሙያ መስክ መሰማራታቸው ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈ ለነገ ስንቅ የሚሆን ተግባራዊ እውቀት እንዲያገኙ ማስቻሉን በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ገለጹ።
በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ብቻ በባህር ዳር ከተማ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ስምንት ሺህ ለሚደርሱ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ፋብሪካዎችን መገንባት ችላለች።
ኢንዱስትሪዎቹ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ በመላክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከማሳደጋቸውም በላይ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ኢዜአ በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ያነጋገራቸው የስራ ዕድል ተጠቃሚ ወጣቶች እንደገለጹት፤ በከተማዋ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ወጣቶች በሙያቸው የስራ ዕድል እንዲያገኙ አስችለዋል።
በአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ የማሽን ባለሙያ የሆነው አባይነህ ታደሰ፤ የተፈጠረለት የስራ ዕድል ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር ብቁ የማሽን ባለሙያ እንዲሆን እንዳገዘው ተናግሯል፡፡
በራቫል ስቲል ማኑፋክቸሪንግ የማሽን ባለሙያ የሆነችውና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዋ ፍሬዘር በላይ፤ በተማረችበት ሙያ መሰማራቷ በቂ ተግባራዊ ዕውቀት እንድትቀስም እንዳስቻላት አስታውቃለች።
በራቫል ስቲል ማኑፋክቸሪንግ የማሽን ባለሙያው አያሉ መንበረ በበኩሉ፤በቴክኒክ ሙያ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱንና እያገኘ ያለው የዕውቀት ሽግግር በቀጣይ በዘርፉ የራሱን የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዳነሳሳው ገልጿል።
በንድፈ-ሀሳብ የተማረውን ዕውቀት በተግባር እየሰራበት መሆኑን የጠቀሰው ወጣት እሸቱ አየለ፤ ራቫል ስቲል ፋብሪካ ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ ስራውን በማስፋፋት ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል እንዲፈጥር ጠንክሮ እንደሚሰራ አረጋግጧል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ብርሃን ንጉሴ በበኩላቸው በከተማዋ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ብቻ ለስምንት ሺህ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡