እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት የአቅመ ደካሞችን ችግር የመፍታት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት የአቅመ ደካሞችን ችግር የመፍታት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል
ድሬደዋ ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በተቀናጀ መንገድ የመፍታት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድሬዳዋ አስተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስገነቧቸው 20 መኖሪያ ቤቶች ዛሬ ተመርቀው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ቤተሰቦች ተላልፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በተቀናጀ የእርስ በርስ መደጋገፍ እና መረዳዳት ባህል እየተከናወኑ የሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በሃገር የብልፅግና ጉዞ ውስጥ መሠረታዊ ስኬት እያመጡ ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶችን በማጎልበት ለብሔራዊ አንድነት መጠናከር የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት አመታት በተከናወኑ ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በርካታ ዜጎች ከዘመመ ጎጇቸው ወደ ተሻለ ህይወት እንዲሸጋገሩ ማስቻሉን አመልክተዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰሩት ልማቶች ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ችግሮችን በላቀ ደረጃ በመፍታት የእርስ በርስ መደጋገፍና መረዳዳትን ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍና ዘመን እንዲሻገሩ እያስቻሉ መሆኑን አንስተዋል።
ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድሬዳዋ የተገነቡት ዘመናዊ ቤቶች የዚሁ መገለጫ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት ከቤቶቹ በተጨማሪ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በድሬዳዋ ከ15 ሺ በላይ ለሆኑ አቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎችና ለገጠር ሴት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግና በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በርካታ ስራዎችን መተግበራቸውን አስታውቀዋል።
ለመጪው ትውልድ መልካም እሴቶችን እያስተማረና እያወረሰ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘላቂ ባህል እንዲሆን ዜጎች ሁሉ ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ሌሎች የፌደራል ተቋማት ክረምት ከበጋ በሚካሄዱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ እያደረጉ ያለው የተቀናጀ ድጋፍና ትብብር ማህበራዊ ችግሮችን በላቀ ደረጃ ለመፍታት እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስጀመሯቸውን ቤቶች አጠናቀው ዛሬ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ማስረከባቸው የዚሁ ማሳያ መሆኑን አንስተው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ቤቶቹ ወገኖቹ ምቹና የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ የሚያስችሉ መሆኑንም ከንቲባው አስታውቀዋል።
በምርቃትና ርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ አምባሳደሮች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ተቋማትና የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ተሳትፈዋል።
የመርሃግብሩ ተሳታፊዎች በቤቶቹ አካባቢ ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።