የዞኑ ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል ረገድ አበረታች ተግባራት እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዞኑ ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል ረገድ አበረታች ተግባራት እያከናወነ ነው
ገንዳውኃ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ ወንጀልን እየተከላከለ የሕብረተሰቡን ደሕንነት በመጠበቅና ለልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ያለፉት ስድስት ወራት የተግባራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ ውይይት አካሄዷል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በወቅቱ እንዳሉት፤ በዞኑ ፖሊስ ወንጀልን እየተከላከለ የሕብረተሰቡን ደሕንነት በመጠበቅ ረገድ አበረታች ተግባራት እያከናወነ ነው።
ፖሊስ የህዝቡን ደህንነትና ሰላም በመጠበቅ ልማት እንዲፋጠን እየተወጣ ያለውን ኃላፊነት ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ተወካይና የዞኑ የወንጀል ምርመራ ምክትል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አንለይ መኮንን በበኩላቸው፤ የዞኑ ፖሊስ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል ሰላምን ለማዝለቅ የተለያዩ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የህዝቡን ደህንነት በመጠበቅ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሰላምን የማስከበር ስራዎች በቁርጠኝነት እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል።
አዲሱ የሪፎርም አተገባበር ፖሊስ ይበልጥ እንዲጠናከር በማድረግ ሀገራዊ ለውጡን ለማሳካት ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ በመስራት ህብረተሰቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
ከዘመኑ ጋር እኩል በመራመድ የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከር እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለፁት ደግሞ በመምሪያው የሰው ኃይል አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር አንዳርጌ አወቀ ናቸው።
የዞኑ ፖሊስ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ህዝቡን በማሳተፍ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።