ቀጥታ፡

የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራው ምርታማነትን ጨምሮልናል- አርሶ አደሮች

ሰቆጣ፤ ታኅሣስ 17/2018 (ኢዜአ)፡- ቀደም ሲል የሠራነው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ የሰብልና የእንስሳት መኖ ምርታማነትን ጨምሮልናል ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የፃግብጅ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የአሥተዳደሩ የ2018 ዓ.ም የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ በፃግብጅ ወረዳ 01 ቀበሌ ማላባ ተፋሰስ ዛሬ ተጀምሯል።
 
በዚሁ ወቅት አርሶ አደር ግርማይ ብዙ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በየዓመቱ ሲያከናውኑት የቆየው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
 
አካባቢያችን ዝናብ አጠር በመሆኑ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራን በልዩ ትኩረት አጠናክረን ቀጥለናል ብለዋል። 
 
የሠራናቸው እርከኖች የአፈር ለምነትና እርጥበት የመያዝ ዐቅም እንዲጨምር በማድረግ ምርታማነታችን እንዲያድግ አስችለዋል ሲሉም ገልጸዋል።


የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራን በማጠናከራቸው የተጎዳው መሬታቸው ማጋገሙን ብሎም ከጎርፍ ስጋት ነጻ መሆኑንና የእንስሳት መኖ ምርታማነትም መጨመሩን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ግርማይ ጌታሁን ናቸው።

በዚህም መሠረት እየተገኙ ያሉ ጥቅሞችን አስፋፍቶ ለማስቀጠል በዘንድሮው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ በንቃት መሣተፍ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደር ደሳለኝ መኮንን በበኩላቸው፤ ጠፍተው የነበሩ ምንጮች በተከናወኑ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ምክንያት ጎልብተው ለመስኖ ልማት መዋላቸውን እና በዚህም ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ዘንድሮ በ366 ተፋሰሶች የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ሥራ እንደሚከናወን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አዲስ ወልዴ ጠቁመዋል።

የተፋሰሶች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በማቋቋም ሕብረተሰቡም እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ በማድረግ ዘላቂ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ እየተሠራ ነው ብለዋል።
 
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ሥራ ዝናብ አጠር ለሆኑ ለአካባቢዎች ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ባለፉት ዓመታት የለሙ ተፋሰሶች ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውንም አስረድተዋል።

ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋጋጥ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራን በይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ሹመት ጥላሁን ናቸው። 
 
በአሥተዳደሩ በዘንድሮው በጋ ከ138 ሺህ በላይ ሰዎችን በማሳተፍ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና  ልማት ሥራ ከ2 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት እንደሚሸፈን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም