ቀጥታ፡

የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ ዲጂታል አገልግሎት ተገልጋዮች ፈጣን መስተንግዶ እንዲያገኙ አስችሏል

ዲላ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦የዲላ ከተማ ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ዲጂታል መደረጉን ተከትሎ ፈጣን አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

አገልግሎቱን በማዘመን ከወረቀት ንክኪ ነጻ መደረጉ ለተጠቃሚዎች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠትና  ገቢን ለማሳደግ ከማስቻሉ ባለፈ የተቋሙን የመፈጸም አቅም ማሳደጉም ተመላክቷል።

የከተማው ነዋሪዎች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዲጂታል መደረጉን ተከትሎ ፈጣንና የተሻለ  አገልግሎት እያገኙ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም በማዘጋጃ ቤቱ አንድ ጉዳይ ለማስጨረስ በቀጠሮ የሚያጠፉት ጊዜና ጉልበትን ከማስቀረቱ ባለፈ ለብልሹ አሰራር የነበረባቸውን ተጋላጭነትም በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ከበደ ወራሳ፤ በወረቀት ያለውን የካዳስተር ይዞታቸውን ወደ ዲጂታል ለመቀየር እንደመጡ ገልጸው፣ በአንድ ቀን ጉዳያቸውን ጨርሰው በመመለሳቸው  መደሰታቸውን ተናግረዋል።


 

ይህም ከዚህ ቀደም አንድ ጉዳይ ለማስጨረስ ለበርካታ ቀናት ሲደርስባቸው የነበረውን እንግልትና ምልልስ በማስቀረት የጊዜና የገንዝብ ብክነትን እንዳስቀረላቸው አንስተዋል።

በመንደራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ተለክቶ ያልተሰራ መንገድ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና በመፍጠሩ ይህን የህዝብ ቅሬታ ይዘው እንደመጡ የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ክፍሌ ሎላ ናቸው።


 

በማዘጋጃ ቤቱ በተጀመረው የፊት ለፊት አገልግሎት የልማት ጥያቄያቸው ለሚመለከተው የሥራ ሃላፊ ቀርቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ  ተስፋ የሚሰጥ ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በማዘጋጃ ቤቱ የተጀመረው ዘመናዊ አገልግሎት ከዚህ ቀደም አንድ ጉዳይ ለማስጨረስ ከቢሮ ቢሮ የቀጠሮ ምልልስ ነበረው፤ በዚህም ጊዜና ጉልበት ይባክን ነበር ብለዋል። 

ማዘጋጃ ቤቱ አገልግሎቱን ማዘመኑ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባለፈ ለብልሹ አሰራር የነበራቸውን ተጋላጭነት በእጅጉ መቀነሱን አስረድተዋል።

የመኖሪያ ቤት ጥያቄያቸውን ይዘው ለረጅም ጊዜ ምላሽ ሳያገኙ ተቸግረው መቆየታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ሃያሌ ሠራዊት የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ማዘጋጃ ቤቱ አገልግሎቱን ማዘመኑን ተከትሎ ጥያቄያቸው ሰሚ አግኝቶ በሚመለከተው የሥራ ክፍል እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

ዲጂታል አገልግሎቱ በማዘጋጃ ቤቱ ከዚህ በፊት የሚነሳውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር የቀረፈ ነው ብለዋል።

ተቋሙ ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ አሰራሩን በማዘመን የግንባታ፣ መሬት አስተዳደር፣ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን ጨምሮ 71 አገልግሎቶችን ዲጂታል ማድረጉን ያነሱት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሃብታሙ ተፈሪ ናቸው።


 

በዚህም አገልግሎቶች ከወረቀት ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ፈጣን አገልግሎት በመስጠት  የተገልጋዩን ማህበረሰብ ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰራው ሥራ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመፍታት ባለፈ የተቋሙን የእለት ገቢና የመፈጸም አቅም አሳድጎታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም