ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ ለዲጂታል ልማት ስኬት የበኩሉን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ ለዲጂታል ልማት ስኬት የበኩሉን እየተወጣ ነው
ጂንካ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለዲጂታል ልማት ስኬት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ገለጸ።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከእውቀት ማእከልነቱ ባለፈ ለባህልና ለተፈጥሮ ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት አካባቢያዊ እውቀትን ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ለማህበረሰብ እመርታዊ ለውጥና ተጠቃሚነት እየሰራ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በተለይም በማህበረሰብ ተኮር ምርምሮች እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ዋና ዋና ዘርፎች መካከል በግብርና እና የእንስሳት ሃብት፣ የቱሪዝም ልማትና የባህል ጥበቃ፣ የማህበረሰብ አገልግሎት የፈጠራ ስራዎች፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እና ሌሎችም ይገኙበታል።
በመሆኑም በዚህ ሰፊ የስራ እንቅስቃሴ ውስጥ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትንና የቀጣይ አቅጣጫዎች በተመለከተ ኢዜአ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ካሳሁን የማነህ (ዶ/ር) አነጋግሯል።
የዲጂታል ኢትዮጵያን እቅድ በማሳካት ሂደት የ5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና አንዱ መሆኑን አንስተው በዚህ ጥረት ውስጥ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የኮደርስ ስልጠና ከወሰዱት የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተማሪዎችና ሰራተኞች መካከል 1 ሺህ 73ቱ ሰርተፍኬት መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሮኒክ ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት 1 ሺህ 879 የሚሆኑ መምህራን፣ተማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች የኮደርስ ስልጠና እየተከታተሉ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በማስፋትና በማበልፀግ በዘርፉ የካበተ ዕውቀት ያለው ዜጋ ለማፍራት የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮደርስ ስልጠና ከወሰዱት መካከል መምህር አስመራ አምዴ፤ የኮደርስ ስልጠና ዘመኑ የሚጠይቀው የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀት መሆኑን ገልጸው እድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በዚህ ዘመን የሰው ሰራሽ አስተውሎትና ሌሎችም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተግባርና የፈጠራ አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአይ ሲቲ ጥገና ባለሙያ ግዛቸው ገንዶሌ፤ የኮደርስ ስልጠና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ብቁ ባለሙያ ሆኖ ለመገኘት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮ ኮደርስ ከተዘጋጁ 4 ኮርሶች 3ቱን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ገልፀው፥በቀጣይም ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል ።
ኮርሱ የያዛቸው ይዘቶች እጅግ ጠቃሚና የዲጂታል ክህሎትን የሚያሰፋ በመሆኑ ሌሎችም የነፃ ስልጠና እድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መክረዋል።