ቀጥታ፡

ከክልሉ ከ6 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል-ባለስልጣኑ

ዲላ ፤ታህሳስ 17/2018 (ኢዜአ):- ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስካሁን ከ6 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ገለጸ።

በክልሉ የቡና ምርት ጥራትና ቁጥጥር ግብር ሃይል በማቋቋም ህገወጥ ንግድና የቡና ብክነትን በመቀነስ የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አማኑኤል ብሩ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ በተያዘው ዓመት ከ131 ሺህ ቶን በላይ ቡና በመሰብሰብ 46 ሺህ 400 ቶን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

ለመሰብሰብ ከታቀደውም እስካሁን ከ52 ሺህ ቶን በላይ ቡና መሰብሰብ መቻሉን አቶ አማኑኤል ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥም የላኪ አርሶ አደሮችን አቅም በማጎልበት ከ10 ሺህ ቶን በላይ ልዩ ጣዕም ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በቅንጅት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ6 ሺህ ቶን በላይ የታጠበና ጀንፈል ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልፀው በቀጣይ ሶስት ወራትም ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በተለይ የቡና ምርት ጥራትና ቁጥጥር ግብረ-ኃይል በማቋቋም ህገወጥ ንግድና የቡና ብክነትን በመቀነስ የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ43 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡም ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም