በዲጂታል ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአገልግሎት አሰጣጥና በሰዎች የኑሮ ዘይቤ ላይ እመርታዊ ለውጥ አምጥቷል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአገልግሎት አሰጣጥና በሰዎች የኑሮ ዘይቤ ላይ እመርታዊ ለውጥ አምጥቷል - ምሁራን
ሐረማያ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ በዲጂታል ልማት ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአገልግሎት አሰጣጥና በሰዎች የኑሮ ዘይቤ ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣቱን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲተገበር ቆይቶ በቅርቡ በስኬት መጠናቀቁ ይታወቃል።
በዚህ የትግበራ ሂደት በቴሌኮም እና ኢንተርኔት መሠረተ ልማት፤ በዲጂታል ክፍያ እና የፋይናንስ ዘርፍ፤ በዲጂታል መታወቂያ እና በተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶች ላይ የሚታዩ ለውጦችና ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በመሆኑም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በይፋ ተጀምሯል።
ከዲጂታል ልማት ትግበራ እና የቀጣዩን እቅድ በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን በዲጂታል ልማት ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአገልግሎት አሰጣጥና በሰዎች የኑሮ ዘይቤ ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር ሚልኬሳ ደጀኔ፤ በዲጂታል ዘርፍ ኢትዮጵያ እመርታዊ ለውጥና ማንሰራራት ላይ መሆኗን ብዙ ማሳያዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
በቴሌኮም እና የኢንተርኔት መሠረተ ልማት፣ በፋይናንስ፣ በተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችና ሌሎችም በዲጂታል አገልግሎት የሚገለጡ ማሳያዎች አሉ ብለዋል።
ከዚህ ስኬት በመነሳትም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ቁልፍ ትልሞች ስኬታማ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮምፒቲንግና ኢንፎርማቲክ ኮሌጅ ምክትል ዲንና መምህር አፈንዲ አብዲ፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማት ማስፋፋት ጋር በተያያዘ የ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ ዝርጋታ ለዘርፉ ልማት ፅኑ መሰረት ማኖሩን ገልጸዋል።
ከዚህ በመነሳት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተደራሽነትን የማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር እና በዜጎችና በተቋማት መካከል መተማመንን የመፍጠር ቁልፍ ተግባር በቀላሉ የሚሳካ መሆኑን አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ይፋ የተደረገው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ያለፈውን ስኬት በማስቀጠል በዘርፉ ልማት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል ነው።