ቀጥታ፡

የመቱ ከተማ የኮሪደር ልማት ገጽታዋን ከመቀየር ባለፈ የስራ እድል ፈጥሯል

መቱ ፤ታኅሣሥ 17/2018 (ኢዜአ)፡- የመቱ ከተማ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር  ባለፈ ለነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን ገፅታ በመቀየር ለቱሪዝም ተመራጭ ከማድረጉ ባለፈ የስራ ዕድልን ፈጥሮልናል።

የኮርደር ልማቱን አስመልክተው ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ የመቱ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ በላይ ተሾመ  በከተማዋ  የተከናወነው የኮሪደር ልማት የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ማድረጉን አስረድተዋል።

በተለይም በከተማዋ የነበሩ የቆሸሹ አካባቢዎችን በማጽዳት ንጹና ውብ ከተማ  በመፍጠር  ጤናማ ዜጋን ለማፍራት ማገዙን  ጠቁመዋል።

የከተማ ኮሪደር ልማት ከተማዋ ለኑሮ ተመራጭ እንድትሆን እያደረጋትና ገጽታዋን  መቀየሩን ያነሱት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ታሪኩ ጌታቸው ናቸው። 

የከተማዋ ልማት ለንግድና ለስራ እድል ፈጠራ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩንም አክለዋል።

በመጀመሪያ ምዕራፍም ስድስት ኪሎ ሜትር የለማ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ደግሞ የመንገድ ልማት፣ የመዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራን በማካተት የአምስት ኪሎ ሜትር ልማት መከናወኑን የገለፁት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ከበደ ነገሱ ናቸው።

የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ የተሳለጠ የትራንስፖርት ፍሰት እንዲኖር ማድረጉንም አክለዋል።

በኮርደር ልማቱ የተሰሩት የመዝናኛና የቆሸሹ ስፍራዎችን የማጽዳት ስራ ዜጎች በጤናማ አካባቢ እንዲኖሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የመንገድ ዳር ልማቱን ከመብራትና ውሀ ዝርጋታ ጋር በቅንጅት መሰራቱ ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረን የመሰረተ ልማት ያለመናበብ ችግርን መቅረፉን አክለዋል።

ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍና ስፖርትን ለማበረታታት የሚያግዙ አነስተኛ የእግር ኳስ ሜዳና መዝናኛ ስፍራዎች በኮሪደር ልማቱ መካተታቸውን ጠቅሰዋል። 

ይህም የከተማዋ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ በማድረግ የነዋሪው  ሁለንተናዊ  ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እገዛ እንደሚኖረውም አውስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም