የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል
ሚዛን አማን፤ ታህሳስ 17/2018 (ኢዜአ):- የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ማስቻሉ ተመላከተ።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በተያዘለት ግብ መሠረት ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ይፋ ባደረጉበት ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚገኙ ሁለት ተቋማት ኃላፊዎች እንዳሉት ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገራችን የተዋወቀው የዲጂታል አገልግሎት ውጤታማ ነው።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚዛን ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ በረከት ትጉ የዲጂታል ሥርዓት ተቋማትን ብሎም ተገልጋይ ዜጎችን ከእንግልት የሚታደግ ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ ውጤት ነው ብለዋል።
ከ5 ዓመታት ወዲህ በዲጂታል ዘርፍ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸው በዚህም አብዛኛው የባንኩ አገልግሎት ዲጂታላይዝ እንዲሆን ማስቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ዓለም በዘርፉ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ የዋጀ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በ2025 የታየው መልካም ተሞክሮ ለ2030ው ዲጂታል ኢትዮጵያ ግብ ትልቅ አቅም አንደሚሆን ጠቁመዋል።
አገልግሎቱን ይበልጥ በማስፋፋት ተደራሽነቱ ላይ መሥራትና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የዓለም ገበያን የሚመጥን ሥራ ሠርቶ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመዲን አወል በበኩላቸው መንግሥት የሕዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ቴክኖሎጂን እያስፋፋ ነው።
ለአብነትም በቅርቡ ወደ ተግባር ገብቶ በርካታ የአገልግሎት ለውጦች እየተመዘገቡበት ያለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከወረቀት ነጻና ዘመናዊ በመሆኑ ድካምን የሚቀንስ ሆኗል ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ወቅቱ የሚጠይው መሆኑን ጠቅሰው በዚህ እሳቤ ማዕከሉ በክልሉ በዲጂታል መንገድ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የዲጂታል ሥርዓት መስፋፋት የዜጎችን የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ብክነትን የመታደግ ፋይዳ የጎላ ሲሆን ይህም በክልሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ35 በላይ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ እየሰጠ ባለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተረጋገጠ ነው ብለዋል።