ቀጥታ፡

የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የቴክኖሎጂ እውቀታችንን በማዳበር ሥራችንን አቀላጥፏል -ሰልጣኞች

ወልቂጤ ፤ ታህሳስ 17/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ ያላቸውን እውቀት በማሳደግ ሥራቸውን ለማቀላጠፍና ውጤታማ ለማድረግ እያገዛቸው መሆኑን በወልቂጤ ከተማ ሰልጣኞች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ በተጀመረው የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ስልጠናው ለ5 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ግብ ተይዟል።

ስልጠናው ዜጎች የተክኖሎጂ እውቀታቸውን ለማሳደግና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን ለማስፋት ያለውን ጠቀሜታ ጉልህ እንደሆነ ታምኖበት ወደተግባር ከተገባ ሦስተኛ ዓመቱን ይዟል።

የኢትዮ-ኮደርስ ስልጥና እየተሰጠባቸው ካሉ አካባቢዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ እንዱ ሲሆን የስልጠናው ተሳታፊዎችም የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማሳደግ ሥራቸውን ለማሳለጥ እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል ወጣት ሄኖክ ወልደጊዮርጊስ እንደገለፀው፣ በአራት የተለያዩ ዘርፎች የቀሰመው የቴክኖሎጂ ክህሎትና እውቀት ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያ እንዲሆን እያስቻለው ነው። 

በተከታታይ የወሰደው ስልጠና እየሰራ ባለበት የመንግስት ተቋም ሥራውን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለማከናወን ከማስቻሉ ባለፈ በእረፍት ጊዜው የግል ሥራ ጭምር በመስራት ተጠቃሚ እንዳደረገው ተናግሯል።

ሌላው ሰልጣኝ ወጣት ወልደተንሳይ ወልደአምላክ በበኩሉ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ያገኘውን ነጻ የስልጠና ዕድል በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎት የሚሠጡ ሶፍትዌሮችን አበልጽጎ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጿል፡፡ 

በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ሮዛ አግዛ በበኩላቸው የወሰዱት ስልጠና የቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕውቀታቸውን በማሳደግ በንግድ ሥራቸው ውጤታማ እያደረጋቸው መምጣቱን ተናግረዋል።

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በጉራጌ ዞን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 58 ሺህ ዜጎች ስልጠናውን እንደወሰዱ የገለፁት ደግሞ የጉራጌ ዞን ሳይንስና ቴክኖሎጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ ናቸው።

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት 24 ሺህ ዜጎችን ለማሰልጠን ታቅዶ እስካሁን ድረስ ለ36 ሺህ ዜጎች ስልጠና መሰጠቱን የገለጹት ሃላፊው፣ "ከእነዚህ ውስጥ 28 ሺህ ዜጎች ስልጠናውን ጨርሰው የምስክር ወረቀት ወስደዋል" ብለዋል።

በኢትዮ ኮደርስ ስልጥና ብዛት ያላቸው ሰልጣኞች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር አዳዲስ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎችን ማልማት እየቻሉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በስልጠናው የሚሳተፉ ዜጎች ቀጥር እያደገ መምጣት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ የሚያበረክተው ፋይዳ የላቀ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ ስልጠናውን በሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ደምስ አመላክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም