ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዲጂታል ክህሎትና ኢኮኖሚ ግንባታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነውበታል - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዲጂታል ክህሎትና ኢኮኖሚ ግንባታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነውበታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዲጂታል ክህሎትና ኢኮኖሚ ግንባታ መሰረት የሆኑ ውጤታማ ተግባራት እንደተከናወኑበት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ምሁራን ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መሳካቱን መግለጻቸው ይታወቃል።
በተለይም በሕዝብ መገልገያ ዲጂታል መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ወሳኝ በሚባል ደረጃ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት መሸጋገሯን ጠቅሰዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተደራሽነትን የማስፋት፣ እኩል እድልን የማመቻቸት፣ በተቋማትና ህዝብ መካከል መተማመንን የመፍጠር ቁልፍ ትልሞች እንዳሉት አብራርተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳሉት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሰረት የጣለና አገልግሎቶችን በማዘመን ተደራሽነትን ማሳደግ ያስቻለ ነው።
በዩኒቨርሲቲው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ሮቦቲክስ ልህቀት ማዕከል ኃላፊ ሀቢብ መሀመድ(ዶ/ር)፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኢንተርኔት ፍጥነትን በማሻሻልና የሞባይልና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ውጤታማነቱን በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
ስትራቴጂው ለዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረት የጣለና በርካታ የመንግስት አገልግሎቶች አሰጣጥን በማዘመን የአገልግሎት ተደራሽነትና ፍጥነት ማሳደጉን ተናግረዋል።
የፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት ቢሮክራሲን ለመቀነስ ሚና እንዳለው አንስተው፤ እንደ አምስት ሚሊየን ኮደርስ ያሉ የዲጂታል አካታችነትና ክህሎትን የሚያሳድጉ መርሃ ግብሮች መተግበራቸውንም አስረድተዋል።
የስትራቴጂው ትግበራ አካታች የፋይናንስ ሥርዓትን በመገንባት፣ የዲጂታል ክፍያና የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም፣ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ፣ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች ስትራቴጂው የተቀመጡለትን ግቦች ማሳካቱን ማሳያ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ለምለም ካሳ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 መሰረተ ልማቶችን ከማሳለጥ፣ አገልግሎቶችን ከማዘመን አኳያ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል።
ምሁራኑ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን፣ መሰረተ ልማቶችን ማጠናከር፣ ፈጠራን ማበልፀግ፣ ለሀገር በቀል ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያስፈልጉ ተቋማት የመገንባት ራዕይን የሰነቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ስትራቴጂውን በውጤታማነት ለመተግበር በዲጂታል መሰረተ ልማትና ክህሎት ግንባታ እና የሳይበር ደህንነት ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልፀዋል።