በሀዋሳ ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል በዓል በስኬት ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል በዓል በስኬት ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ፖሊስ
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ በሀዋሳ ከተማ ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ በስኬት ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ግርማ ማቴዎስ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማዋ ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ታዳሚዎች ሌሎች እንግዶች በሚገኙበት በድምቀት ይከበራል፡፡
በመሆኑም በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ በስኬት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመው ከክልሉና ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ከሐይማኖት አባቶችና ሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከበዓሉ ቀደም ባሉ ቀናት እንዲሁም በበዓሉ ዕለት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር በቂ የቁጥጥር ሥራ ለመስራት ከወዲሁ የሰው ኃይል ምደባ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
በዓሉ በሚከበርበት ሥፍራ እንዲሁም እንግዶች በሚያርፉባቸው እና በሚዝናኑባቸው ቦታዎች ሁሉ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ቋሚና ተንቀሳቃሽ ጥበቃ ሥራን የሚያከናውኑ የፀጥታ አካላት ስምሪት እንደተደረገም አክለዋል፡፡
በዕለቱ የስርቆትና መሠል ወንጀሎች ተፈፅመው ከተገኙ አፋጣኝ ፍትሕ መስጠት እንዲቻል መርማሪ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግና ዳኞች የተዋቀሩበት ጊዜያዊ ችሎት በበዓሉ ሥፍራ እንደሚቋቋምም ጠቁመዋል፡፡
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ መቅደስ ሁሪሶ በበኩላቸው በዓሉ በርካታ እንግዶች የሚስተናገዱበት በመሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
እንግዶች በሚስተናገዱባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከሆቴልና የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም ከሌሎች የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በቂ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡