የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተኪ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እያመረተ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተኪ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እያመረተ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ የቡልቡላ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተኪ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እያመረተ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ መንግስቱ ረጋሳ፣ የቡልቡላ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመርቆ ስራውን የጀመረው በ2013 ዓ.ም እንደሆነ አስታውሰዋል።
በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለማስገባት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ሰፋፊ ተግባራት ሲከናወኑ እንደቆዩም አውስተዋል።
ባለሀብቶች በፓርኩ ገብተው እንዲያለሙ የማስተዋወቅ ስራዎችም እንደተሰሩ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም በፓርኩ 45 ባለሀብቶች መግባታቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥ አስር ባለሀብቶች የተለያዩ የግብርና ምርቶችን እያቀነባበሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ማምረት የገቡ ባለሀብቶች ዘይትን ጨምሮ ሌሎች ተኪ ምርቶችን በማምረት ለገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ አጠቃላይ ለባለሀብቱ ማምረቻ ካዘጋጀው 136 ሄክታር መሬት ውስጥ 75 ሄክታር መሬት ለባለሀብቱ በሊዝ መሰጠቱንም አክለዋል።
ለቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርና ምርት ጥሬ ዕቃ ለማቅረብ የተዘጋጁ የገጠር ሽግግር ማዕከላት እንዳሉም አንስተዋል።
የገጠር ሽግግር ማዕከላቱም በሻሸመኔ፣ ዶዶላ፣ ኢተያ፣ ባሌ ሮቤ እና ወለንጪቲ ከተሞች የተገነቡ ሲሆን፤ አርሶ አደሩ ከሽግግር ማዕከላቱ ጋር እንዲተሳሰሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ማዕከላቱ ከግብርና ምርት በተጨማሪ ፓስታ፣ መካሮኒና ሌሎችም የታሸጉ ምግብ ነክ ምርቶችን እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የአካባቢው አርሶ አደሮችን ጨምሮ ሌሎች የስራ እድል ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባለፈ የአካባቢው ማሕበረሰብ ከሚመረተውም ጥራቱን የጠበቀ ምርት እያገኘ መሆኑን አብራርተዋል።