መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልትንና የጊዜ ብክነትን አስቀርቷል- ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልትንና የጊዜ ብክነትን አስቀርቷል- ተገልጋዮች
ሻሸመኔ፤ ታኅሣስ 17/2018 (ኢዜአ)፡- የሻሸማኔ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ፣ እንግልትን ያስቀረና ጊዜን የቆጠበ ነው ሲሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
በአንድ ስፍራ የተሟላ፣ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ማግኘታቸው፤ ይባክን የነበረ ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪን እንዳስቀረላቸው ተገልጋዮቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ማዕከሉ ቀደም ሲል በከተማዋ የመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት የነበረ እንግልትን በማስቀረት በሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻሉንም አንስተዋል።
የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ገመቹ ነቢይ በበኩላቸው፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይነሳ የነበረ የሕዝብ ቅሬታ ማዕከሉ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ መቀረፉን አረጋግጠዋል።
በማዕከሉ በ26 ተቋማት 111 አገልግሎቶች በተሟላ መልኩ ለሕብረተሰቡ እየቀረቡ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የጥራትና የፍጥነት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታቱን ያረጋገጡት ደግሞ የሻሸማኔ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነ ተክለጊዮርጊስ ናቸው።
መሰል ማዕከላት በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚስፋፉም አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ ሀገር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ባስጀመሩበት ወቅት፤ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የሕዝብን ቅሬታ ለመፍታት ግብ ይዞ ወደ ሥራ የገባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች እንደሚስፋፋ መግለጻቸው ይታወሳል።