በበጋ መስኖ ስንዴ የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እመርታዊ አቅም እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በበጋ መስኖ ስንዴ የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እመርታዊ አቅም እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ በበጋ መስኖ ስንዴ የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እመርታዊ አቅም እየተፈጠረ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በ2018 ዓ.ም የበጋ መስኖ ልማት መርሃ ግብር እስከ አሁን 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሔክታር መሬት በዘር መሸፍኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው።
በ2011 ዓ.ም በ3ሺህ 500 ሔክታር መሬት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ማሳን ወደ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር መሬት በማስፋት ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያስቻለ የምርት አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።
በ2017 ዓ.ም በ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ 128 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰብ ያስቻለ ስኬት መመዝገቡንም አስታውሰዋል።
በተያዘው ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መርሃ ግብርም 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር መሬትን በሰብል በመሸፈን 175 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም እስከ አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሔክታር የእርሻ ማሳን በማዘጋጀት ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሔክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም አርሶ አደር የበጋ መስኖ ስንዴን ባህል በማድረጉ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እመርታዊ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሚካሄድባቸው ሁሉም አካባቢዎች የመስኖ መሠረተ ልማት የመዘርጋት፣ የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መሰራጨቱን አብራርተዋል።
በአርሶ አደሮች ዘንድ የተፈጠረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ግንዛቤና ባህል ምርታማነትን በማሻሻል ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮችም በበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እያደገ ስለመምጣቱ አብነቶች ናቸው።
አርሶ አደር ሲሳይ ደስታ፤ በበጋ መስኖ ሜካናይዜሽን ሥርዓት በመንግስት የተደረገላቸው ድጋፍ በስንዴ ምርት ከራሳቸው አልፈው ለገበያ ማቅረብ የቻሉበትን አመርቂ ውጤት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ጌቱ ደሳለኝ፤ የግብርና ልማት ባለሙያዎች በሜካናይዜሽን አስተራረስ ዘዴ የሰጧቸው ሙያዊ ድጋፍ በኩታ ገጠም ሰብል ልማትና ምርት አሰባሰብ ላይ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።