በዞኑ የደረሰ ሰብል ባልተጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በቅንጅት እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የደረሰ ሰብል ባልተጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በቅንጅት እየተሰበሰበ ነው
ጊምቢ፤ ታኅሣስ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በ2017/18 የመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው 483 ሺህ ሔክታር በ392 ሺህ 267 ሔክታር ላይ የለማው ሰብል መሰብሰቡን የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ፈይሳ ሀምቢሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አርሶ አደሮች በአደረጃጀትና ቤተሰቦቻቸውን በማቀናጀት ጭምር ሰብላቸውን እየሰበሰቡ ነው ብለዋል።
በምርት ዘመኑ በሰብል ከለማው መሬት ከ14 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
የጊምቢ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ካሊድ አብዱ በግማሽ ሔክታር ላይ ያለሙትን በቆሎ በአግባቡ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።
በኩታ ገጠም ያለሙትን የዳጉሳና በቆሎ ሰብል መሰብሰባቸውን የገለጹት ደግሞ የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ታዬ ኦላኒ ናቸው፡፡
ሰብሉ በዝናብ እንዳይበላሽ ብሎም ለብክነት እንዳይዳረግ በግብርና ባለሙያዎች እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍና ክትትል መሠረት መሰብሰባቸውንም ነው አርሶ አደሮቹ የገለጹት።