ቀጥታ፡

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያገኘውን የእንስሳት መኖ የሳር ዝርያ እያስፋፋ ነው

ሐረማያ፤ ታህሳስ 17/2018 (ኢዜአ)፡- ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያገኘውን  የእንስሳት መኖ የሳር ዝርያ እያስፋፋ  መሆኑን አስታወቀ።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሃብት አያያዝና አካባቢ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ  ዳርጎ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው  “ላይም ግራስ” የተሰኘን የእንስሳት መኖ የሳር ዝርያ በምርምር አግኝቷል።

በምርምር የተገኘውን የሳር ዝርያ በምስራቅ ሐረርጌ ዞንና  ማያ ከተማ መስተዳድር በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች  እና አራት ቀበሌዎች በአርሶ አደር ግብርና ማሰልጠኛ ማዕከላትና በአርሶ አደር ማሳ ላይ እያስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሳር ዝርያው በአንድ ሽህ አባወራ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ መስፋፋቱን አመልክተዋል።

ቀደም ሲል በአካባቢው የነበሩት የሳር ዝርያዎች እርጥበትንና ሰፋፊ ቦታዎችን  በከፍተኛ ሁኔታ  የሚፈልጉና የሰብሎችን ንጥረ ነገርና ውሃ የሚሻሙ መሆኑን ጠቁመው “ላይም ግራስ”  የተሰኘው የሳር ዝርያ   ውርጭ፣ የዝናብ እጥረትና ድርቅን  በመቋቋም በአነስተኛ መሬት ብዛት ያለው የሳር መኖ የሚያስገኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የሳር ዝርያው ከአንድ ወር እስከ አንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ፈጥኖ የሚደርስ መሆኑንም ጠቁመው በተጠቀሱት ባህርያቱ በሐረርጌ አካባቢ የሚስተዋለውን የእንስሳት መኖ ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ገልጸዋል። 

የሳር ዝርያው ለእንስሳት መኖነት  ከእርጥብነት በተጨማሪ  በድርቆሽነትም የሚያገለግል መሆኑን ጠቁመው በከብት እርባታና ማድለብ  ስራ የተሰማሩ አካላትን ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል፡፡ 

በተለይም የሳር ዝርያው በያዘው ንጥረ ነገር ከእንስሳት ሃብት የሚገኘውን የስጋ  ምርታማነትን የሚጨምር መሆኑም  በምርምሩ በተካሄደ  የከብቶች ምገባ መረጋገጡን አመልክተዋል።

እንዲሁም ዘሩን በማምረትና ለገበያ በማቅረብ በገቢ ምንጭነት በመጠቀም  የተሻለ ጥቅም ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የሳር ዝርያውን ወደ አርሶ አደሩ በማስፋፋት ከእንስሳት ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ የማሳደግ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም