ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ የ”ቦክሲንግ ደይ” መርሃ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ):- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሃ ግብር በማንችስተር ዩናይትድ እና ኒውካስትል ዩናይትድ መካከል ዛሬ ይካሄዳል።

ጨዋታው ምሽት አምስት ሰዓት በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ይደረጋል። 

ማንችስተር ዩናይትድ በ26 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ኒውካስትል ዩናይትድ ደግሞ በ23 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። 

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 60 የርስ በርስ ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 33 ጊዜ ሲያሸንፍ ኒውካስትል ዩናይትድ 11 ጊዜ ድል ቀንቶት 16 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

ማንችስተር ዩናይትድ በጨዋታዎቹ 117 ግቦችን ሲያስቆጥር ቦርንማውዝ 68 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል።

ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በነበራቸው የእርስ በእርስ ግንኙነት ኒውካስትል ዩናይትድ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል። 

ወጥ ብቃት ማሳየት የተሳነው ማንችስተር ዩናይትድ ሶስት ነጥብ ማግኘት ወደ አሸናፊነት እንዲመለስ ያደርገዋል። 

ኒውካስትል ዩናይትድ ከሁለት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

የ47 ዓመቱ እንግሊዛዊ አንቶኒ ቴይለር ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

‘ቦክሲንግ ዴይ’ የፈረንጆች ገና በተከበረ በቀጣዩ ቀን ያለው ስያሜ ሲሆን በገና ወቅት በርካቶች ስጦታ የሚሰጣጡት በሳጥን(Box) መሆኑን ተከትሎ በዛን ወቅት የሚደረጉ ጨዋታዎችም ቦክሲንግ ዴይ ተብለው ተሰይመዋል።

‘ቦክሲንግ ዴይ’ በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩ ዜጎች የበጎ አድራጎት እና መልካም ተግባር የሚከውኑበት ዕለት ነው።

ክለቦች በቦክሲንግ ዴይ ጨዋታዎች የትኬት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ በማድረግ በተለይ ሕጻናት ስታዲየም እንዲገቡ ያበረታታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም