የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡-የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ።
"ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ስለ ኢትዮጵያ የውይይት መድረክ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ ወረዳ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት ሥፍራ ተካሂዷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ኃይሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ብልጽግና በተግባር የሚያሳይ ፕሮጀክት ነው።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የህዝቦች አብሮነት የተንጸባረቀበትና ለትውልድ የሚተላለፍ የታሪክ አሻራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ለኢንዱስትሪ ምርታማነትና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በተለይም ዲጂታላይዜሽንን እውን በማድረግ በሁሉም ዘርፎች ስኬታማ ስራዎች እንዲሰሩ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የከፍታ መገለጫ ነው ብለዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ኩራትና የትውልዱ ታላቅ ቅርስ መሆኑን አውስተው፤ ለቱሪዝም ልማት የማዋል ተግባር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያስረዱት።
ግድቡ ለቱሪዝም ዘርፉ ይዞ የመጣውን እድል አሟጦ ለመጠቀም በዘርፉ አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ተጨማሪ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማለም እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ያላትን ሃብት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ በተግባር ያሳየና መሰረታዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ የይቻላል መንፈስን የፈጠረ ነው።
በግድቡ ግንባታ የታየውን ህብረት በሌሎች ስራዎች ላይ እውን ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ በሰጡት ማጠቃለያ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን የሃይል አቅርቦት እንዲያድግ እድል መፍጠሩን ጠቁመው፤ ይህም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት፣ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬታማነትና ለሌሎች ዘርፎች ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያን ማንሰራራት በተግባር በማሳየት ረገድ ትልቅ ምሳሌ መሆን መቻሉን ጠቅሰዋል።