ቀጥታ፡

ህንድ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬታማነት ያላትን ሰፊ ተሞክሮ ታጋራለች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ ህንድ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬታማነት በዲጂታል የህዝብ አገልግሎት መሰረተ ልማት ያላትን ሰፊ ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መሳካቱን መግለጻቸው ይታወቃል።

በተለይም በሕዝብ መገልገያ ዲጂታል መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ወሳኝ በሚባል ደረጃ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት መሸጋገሯን ጠቅሰዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን መሠረት በማድረግ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ ተደራሽነትን ማስፋት፣ እኩል እድልን በማመቻቸትና በተቋማትና ህዝብ መካከል መተማመንን የመፍጠር ቁልፍ ትልሞች እንዳሉት አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በሀገሪቱ የሚተገበሩ የዲጂታል ዕቅዶችን ለመወጠን መሰረት የተጣለበት ነው።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም የ5ጂ ኔትወርክንና የፋይዳ መታወቂያን በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

ይህም የባንክ አገልግሎትን በመላ ሀገሪቱ በማዳረስ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥና ዜጎች በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ እንዲችሉ አስተዋፅኦ እንዳለው አንስተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማደጉ የሀገራቱን ትብብር እንደሚያጠናክር ጠቅሰው፤ በጋራ ከሚሰራባቸው ዘርፎች አንዱ ዲጂታላይዜሽን መሆኑንም ገልፀዋል።

ህንድ በዲጂታል መሰረተ ልማት ያላትን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ በማጋራት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗንም አብራርተዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጠንካራ የዲጂታል መሰረተ ልማት በመዘርጋት ሀገሪቱን የሚለውጥ መሆኑን አንስተው ህንድ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ስኬታማ ጉዞ የድርሻዋን እገዛ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም