ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከማሳደግ ባለፈ ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከማሳደግ ባለፈ ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።

"ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው ስለ ኢትዮጵያ የውይይት መድረክ በሕዳሴ ግድብ ተካሂዷል።


 

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በውይይቱ ላይ የሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ኃይል ትስስርና ለኢኮኖሚ ግንባታ ባለው ፋይዳ ላይ ትኩረት ያደረገ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጸሁፍ አቅርበዋል።

ኢንጂነር አሸብር እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት በእጥፍ እንዲጨምር አስችሏል።

የኢትዮጵያ ኃይል የማምረት አቅም ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት ያልበለጠ ነበር ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ሀገራዊ ኃይል የማንጨት አቅም ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለኬኒያ፣ ጁቡቲ፣ ሱዳን በከፊል ለታንዛኒያ ኃይል እያቀረበች መሆኑን አስታውሰው፤ ወደ ውጭ ከሚላከው 51 በመቶ የሚሆነው ኃይል የሚሸፍነው ከህዳሴ ግድብ የሚመነጨው ኃይል መሆኑን አስረድተዋል።

ለደቡብ ሱዳንና ለሶማሊያም በተመሳሳይ ኃይል ለማቅረብ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ከኃይል አቅርቦት የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰው፤ የግድቡ እውን መሆን ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የውጭ ባለኃብቶች ለመሳብ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች 2500 ሜጋ ዋት ኃይል ያስፈልጋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው እያደገ የመጣው የኃይል አቅርቦት ፍላጎትን ለማሟላት በሚደረገው እንቅስቃሴ የሕዳሴ ግድብ ወደ ሥራ መግባት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲያማትሩ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም