ሱዳን፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ፤ በአፍሪካ ዋንጫው የሚሳተፉ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት - ኢዜአ አማርኛ
ሱዳን፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ፤ በአፍሪካ ዋንጫው የሚሳተፉ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ሲሆን 24 ሀገራት በስድስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። ከተሳታፊዎቹ መካከል ሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ናቸው።
በምድብ አምስት የምትገኘው ሱዳን ከአልጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ተደልድላለች። ሱዳን በአፍሪካ ዋንጫው ስትሳተፍ የአሁኑ ለ10ኛ ጊዜ ሲሆን ውድድሩ ሲጀመር መስራች ከነበሩ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
እ.አ.አ በ1957 የተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ የተደረገው በሱዳን ሲሆን በወቅቱ ግብጽ ኢትዮጵያን 4 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
ሱዳን እ.አ.አ በ1970 ያዘጋጀችው ሰባተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ጋናን በፍጻሜው በማሸነፍ በሀገሯ ያስቀረች ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑ እ.አ.አ በ2021 በካሜሮን በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በድጋሚ ወደ ውድድሩ ተመልሷል።
በምድብ ሶስት ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ይገኛሉ። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራቱ ከናይጄሪያ እና ቱኒዚያ ጋር የተደለደሉ ሲሆን ዩጋንዳ በአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ ለስምንተኛ ጊዜ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1962 ባዘጋጀችው ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበር። በወቅቱ ለደረጃ ደርሳ በቱኒዚያ ሽንፈት ያስተናገደችው ዩጋንዳ አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ጋና እ.አ.አ በ1978 ባዘጋጀችው 11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዩጋንዳ ለፍጻሜ ደርሳ በአዘጋጇ ሀገር የ2 ለ 0 ሽንፈትን አስተናግዳ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ውጤት በተሳትፎ ታሪኳ የተሻለ የሚባለው ነው።
ግብጽ እ.አ.አ 2019 ባዘጋጀችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዩጋንዳ ወደ ጥሎ ማለፍ ብትገባም 16 ውስጥ በሴኔጋል 1 ለ 0 ተሸንፋ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፍ አልቻለችም።
ታንዛንያ በአፍሪካ ዋንጫው ስትሳፍ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን እ.አ.አ በ1980 ናይጄሪያ ባዘጋጀችው 12ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፋ ከምድቧ ማለፍ ሳትችል ቀርታ ነበር። ታንዛንያ ከሁለት ዓመት በፊት በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፋ ከምድቡ ማለፍ ሳትችል ቀርታለች። ግብጽ እ.አ.አ በ2019 ባዘጋጀችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይም ተሳትፎ አድርጋለች።
በአፍሪካ ዋንጫው በምድብ አምስት የምትገኘው ሱዳን ከአልጄሪያ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታዋን አድርጋ 3 ለ 1 ተሸንፋለች።
በምድብ ሶስት የመጀመሪያ መርሃ ግብር ታንዛያ በናይጄሪያ 2 ለ 1 ስትሸነፍ ዩጋንዳ በቱኒዚያ የ3 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዳለች።
በምድብ አምስት ሱዳን ከኢኳቶሪያል ጊኒ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ትጫወታለች። በምድብ ሶስት ዩጋንዳ ከታንዛንያ ቅዳሜ ምሽት 2 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በየምድባቸው ከጠንካራ ቡድኖች የተደለደሉ ሲሆን ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ከፊታቸው ፈተና ይጠብቃቸዋል።