ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢኩስታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋምን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 16/2018(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሸገር ከተማ ለቡ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢኩስታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ዛሬ ጎብኝተዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ልማት የምታደርገው አስተዋጽዖ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የቀየረ ነው ብለዋል።


 

ቤተ ክርስቲያኗ በትምህርት፣ በጤና፣ በመጠጥ ውኃ ልማትና በወጣቶች የቴክኒክ ሥልጠናዎች የምታደርጋቸው የልማት ድጋፎች ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ አበርክቷቸው ታላቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ በተለይም በሕክምናው ዘርፍ የኢትዮጵያን የመመርመርና የማከም ዐቅም ያሳድጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁሉም በላይ የተቋሙ ንጽሕና እና ጽዳት ለብዙ ተቋማት ምሳሌ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።


 

አስፈላጊ ሁኔታዎች ተሟልተው በቶሎ ሁለንተናዊ አገልግሎቱን እንዲጀምር በመንግሥት በኩል የሚፈለጉ ድጋፎች እንደሚደረጉ አመልክተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተቋሙ የሚሆን መሬት የሰጠውን የኦሮሚያ ክልልን፤ እንዲሁም ተቋሙን በዘመናዊ መሣሪያዎች ለማደራጀት ላገዙ በሙሉ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም