ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እያደረገ ያለው ጥረት ሊጠናከር ይገባል

ድሬደዋ፣ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፡- ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል  የፕላንና  ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ዩኒቨርሲቲው ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባቸውን የተለያዩ የልማት  ፕሮጀክቶች ዛሬ አስመርቆ  ስራ አስጀምሯል።


 

የፕላንና  ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ፣ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዑባህ አደም (ዶ/ር) እና ሌሎች የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ፕሮጀክቶቹን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ተመርቀው ወደ አገልግሎት ከተሻገሩት ፕሮጀክቶች መካከል  የዩኒቨርስቲው መምህራን ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና የህፃናት ማቆያ፣ የ2 ነጥብ 7 ኪሎሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድና  የመንገድ መብራቶች ተጠቃሽ ናቸው።

በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው የኤሌክትሮ መካኒካል ቀሪ መሠረተ ልማቶች፣ የተማሪዎች የመኖሪያና የመፀዳጃ ህንፃዎች እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃዎች ይገኙበታል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትርና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው ያስመረቃቸው ፕሮጀክቶች  የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ ዩኒቨርስቲው የተጠለበትን አገራዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣም የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው በዚህ እረገድ ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይ የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንግስት የዜጎችን መሠረታዊ የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት ለማሟላት እያከናወነ የሚገኘው ዘርፈ ብዙ የተቀናጁ ጉዞዎች ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው የመምህራንን አቅም ለመገንባትና የማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት አገራዊ ትልሞችን ለማሳካት መሠረታዊ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

በዛሬ ዕለት የተመረቁት የመምህራን ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዚሁ ማሳያ ናቸው ብለዋል።


 

ፕሮጀክቶቹ ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮውን ለመወጣት እያደረገ የሚገኘውን አበረታች ስራ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ወሳኝ አበርክቶ እንዳላቸው የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኡባህ አደም (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው እንደ አገር የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በጥራት ከዳር ለማድረስ እያከናወነ የሚገኙት ተግባራት ፍሬያማ መሆናቸውን ተናግረዋል ።


 

ፕሮጀክቶቹ የመምህራና የተማሪዎችን ጥያቄዎች በመፍታት ጥራት ያለው ትምህርትና ትውልድ የመፍጠሩን ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን እንደሚያስችሉ ጠቅሰዋል።

በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች፣ የተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም