በዞኑ የገጠር ኮሪደር ልማትን ከቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር በማስተሳሰር ለማስፋፋት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የገጠር ኮሪደር ልማትን ከቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር በማስተሳሰር ለማስፋፋት እየተሰራ ነው
ዲላ፤ታህሳስ 16/2018 (ኢዜአ):- በጌዴኦ ዞን የገጠር ኮሪደር ልማትን ከቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር በማስተሳሰር ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የከተማ የኮሪደር ልማት አፈጻጸም ማጠናከሪያና የገጠር የኮርደር ልማት ትግበራ እንዲሁም ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን ማዘመን ዙሪያ የምክክር መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
በዘህ ወቅት በብልጽግና ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ኢንጂነር ተመስገን ጥላሁን እንዳሉት፤ ዲላን ጨምሮ በዞኑ አምስት ከተሞች ሕብረተሰቡን በማስተባበር የተተገበረው የኮሪደር ልማት ወደ ገጠር ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ነው።
የገጠር ኮሪደር ልማት ንጹህ የመኖሪያ አካባቢና የጤና አገልግሎት እንዲሁም ታዳሽ ሃይልን ተደራሽ ማድረግን ጭምር ያካተተ ነው ብለዋል።
በተለይ የገጠርና ከተማ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ የዘላቂ የልማት ግቦችን በዞኑ ባጠረ ጊዜ ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ በትኩረት ይተገበራል ነው ያሉት።
የገጠር ኮሪደር ልማትን ከቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር በማስተሳሰር ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ረዲኤት ክፍሌ ናቸው።
በከተማ የታየው የሕብረተሰብ ተሳትፎ በገጠሩም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።
በዞኑ የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ በበኩላቸው፤ ወረዳው የጌዴኦ ባሕላዊ መልከዓ ምድር አካል የሆነ "የቱቲት " መካነ ቅርስ ትክል ድንጋዮና የጥምር ግብርና መገኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የአካባቢውን ተፈጥሮዊና የመስህብ ቦታዎችን በሚያጎላ መልኩ ሞዴል የገጠር የኮሪደር ልማት ተግባራዊ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
ይህም ወረዳውን ከቡና ልማት በተጨማሪ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም አውጥቶ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የዞኑና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።