ሀገር በቀል እውቀቶችን በጥናትና ምርምር በማላቅና በመጠበቅ ጥቅም ላይ ለመዋል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል እውቀቶችን በጥናትና ምርምር በማላቅና በመጠበቅ ጥቅም ላይ ለመዋል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
አምቦ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ ሀገር በቀል እውቀቶችን በጥናትና ምርምር በማላቅና በመጠበቅ ጥቅም ላይ ለመዋል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴር እና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ትብብር "ሀገር በቀል እውቀቶች ለዘላቂ ልማትና ሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷዋል።
በሲምፖዚየሙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራንና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሃዲ፤ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማጥናትና በማልማት የሀገር ሃብት ሆነው እንዲዘልቁ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ሀገር በቀል እውቀቶችን በሚፈለገው ልክ በመጠበቅና በማጎልበት ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ በኩል ውስንነቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
አሁን ግን ሀገር በቀል እውቀቶችን በጥናትና ምርምር በማላቅና በመጠበቅ ለመጠቀም የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲፖዚየሙ ዋነኛ አላማም በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን በጥናትና ምርምር ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አንስተው ሀገር በቀል ሃብቶችን በማልማትና በማካበት ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የቀጥላል ብለዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ብርሃኑ ከበደ(ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተለይ ባህላዊ መድሃኒቶች በጥናትና ምርምር ታግዘው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲፖዚየሙ መካሄድ በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶችን በጋራ ወደ ውጤት ለመቀየር ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑ ከተሳታፊዎች ተነስቷል።
በመሆኑም በዚሁ ጉዳይ ላይ በምሁራኑ የቀረቡ የጥናት ውጤቶችን ደምሮ ጥቅም ላይ ለማዋል መዘጋጀት እንደሚገባም ተመላክቷል።