ቀጥታ፡

የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ቡታጅራ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን የብድር አቅርቦት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአርሶ አደሮች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማስጀመሪያ ንቅናቄ በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ዲጂታል ኢኮኖሚ በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አማካኝነት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን፣ ግብይቶችን ለማሳለጥና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስርአት ነው።

በሚኒስቴሩ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ትግስቱ ገብረመስቀል እንደገለጹት፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ አካል የሆነውን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎትን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት በማለም የፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል፡፡

በዚህም መንግስት ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን በማድረግ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት የጀመረውን ጥረት በማሳካት የአርሶ አደሩን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በብሔራዊ የመሬት አስተዳደር መረጃ ስርዓት በ516 ወረዳዎች ከ32 ሚሊየን በላይ ማሳ መመዝገቡንና የመሬት ባለቤትነት ምስክር ወረቀት ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ ባስመዘገበው የመሬት መጠንና ሀብት የገንዘብ ብድር እንዲያገኝ የፋይዳ መታወቂያ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በቀጣይ ሦስት ወራት 12 ሚሊየን በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የብሔራዊ መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ይግለጡ አብዛ በበኩላቸው፣ በክልሉ ዜጎች ባሉበት ሆነው የመንግሥት አገልግሎትን እንዲያገኙ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ለአብነት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ብሔራዊ መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ በዘንድሮው ዓመት 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ሰዎች የፋይዳ መታወቂያ እንዲያገኙ መታቀዱን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ 1 ሚሊየን የሚጠጋ የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አህመድ ሀቢብ የፋይዳ መታወቂያ ከፋይናንስና ግብዓት አቅርቦት ረገድ የሚነሱ ውስንነቶችን በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ተደራሽነትን መቶ በመቶ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ዋና አስተባባሪ ደጀኔ ገብሬ ናቸው፡፡

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆኑ 90 ሚሊየን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን ከ30 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፣ አርሶ አደሩን ጨምሮ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም