የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡባቸው አስራ ሰባት አካባቢዎች በጥናት ተለይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡባቸው አስራ ሰባት አካባቢዎች በጥናት ተለይተዋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ግንባታቸው የተጠናቀቁ የቡሬ፣ ቡልቡላና ይርጋለምን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡባቸው አስራ ሰባት አካባቢዎች በጥናት መለየታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግል አልሚዎችን ያሳተፈ የኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ የሚገነቡባቸው አስራ ሰባት አካባቢዎች በጥናት ተለይተዋል።
ከእነዚህም መካከል የቡሬ፣ ቡልቡላና ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለሀገር ውስጥ ገበያ ማደግ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለገቢ አሰባሰብ ማደግ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ብለዋል።
የትኛውም ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በሚያደርጋቸው ጥረቶች የምርቶች ጥራትና ስብጥር፣ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለገበያ ማቅረብና የአመራረት መንገዶች ከመመዘኛ መስፈርቶች እንደሚመደቡ ጠቅሰዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎችን በፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግስት በፓርኮቹ የፈጠራቸውን እምቅ እድሎችና ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በፎረሙ የተገኙ ባለሀብቶችም በተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ከፋይናንስ አቅርቦት፣ ከተቋማት ቅንጅት፣ ከመደራጀትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ በበኩላቸው፤ ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ ከባቢን ለመፍጠር የህጎችና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን መተግበር መጀመሯን አስታውሰው፤ የተፈጠሩ እድሎችን በስፋት ለመጠቀምና ተወዳዳሪ ለመሆን ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አምራቾችም በተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተፈጠሩ እድሎችን እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ቀደም ሲል ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን መፍታት በመቻሉ በርካታ ባለሀብቶች በፓርኮቹ እየተሰማሩ ነው ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል ከፋይናንስ ተቋማት፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።