በእንስሳት ሃብት ልማት የአርሶ አደሮችን ምርታማነትና ዘላቂ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በእንስሳት ሃብት ልማት የአርሶ አደሮችን ምርታማነትና ዘላቂ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ባቱ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ በእንስሳት ሃብት ልማት የአርሶ አደሮችን ምርታማነትና ዘላቂ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ምርታማነታቸውና ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ የተሻሻሉ የላም ዝርያዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ለሚገኙ አርሶ አደሮች ተላልፈዋል።
በመርሃ ግብሩ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሣ(ዶ/ር)፤ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት ብቻ 5 ሚሊየን የወተት ላሞችን ለማዳቀል ታቅዶ እስካሁን 2 ሚሊየን ማዳቀል መቻሉን ጠቅሰው በዘርፉ ልማት በትኩረት በመስራት የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን ከማሳደግ አንፃር በዶሮና የዓሣ ልማት እንዲሁም የንብ ማነብ ዘርፎች ላይ ተመሳሳይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ በዝሪያ ማሻሻያ ላይ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ ጌቱ ገመቹ ናቸው።
ባለፈው ዓመት በክልሉ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ላሞችን በማዳቀል ከ400 ሺህ በላይ ዝርያቸው የተሻሻሉ ጥጆች መወለዳቸውን አንስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ላሞችን በሰው ሰራሽና በመደበኛ የማዳቀል ስራ በብዛት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የዘርፉን ልማትና ተጠቃሚነት የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው የዛሬው መርሃ ግብርም የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ፤ በዞኑ በተለይም የሌማት ትሩፋትን በማስፋፋትና ሌሎች የልማት ስራዎችን አቀናጅቶ በመስራት ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮው ዓመት በዞኑ ከ59ሺህ በላይ ሰዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አንስተው የእስካሁኑ ሂደት ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ከእንስሳት ሃብት ልማት በተጨማሪ በበጋ መስኖ ስንዴ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎች የሰብል አይነቶች ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።