በክልሉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት እንዲችሉ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት እንዲችሉ ትኩረት ተደርጓል
ጎንደር፤ ታህሳስ 16/2018 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት እንዲችሉ ትኩረት መደረጉን የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በአዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና በጎንደር ከተማ ዛሬ አስጀምሯል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ስብሁ ገበያው (ዶ/ር) በስልጠና ማስጀመሪያው ላይ እንደገለጹት አዲሱ የስልጠና ፖሊሲና ስትራቲጂ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል በማምረት ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችል ነው።
ስልጠናው ፖሊሲና ስትራቴጂው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ ሀገር በቀል እውቀትን ማጎልበት ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ወጣቱን ትውልድ መጥቀም ዓላማው ያደረገ ነው ብለዋል።
የአለም ሀገራት እድገትና ብልጽግናቸውን ማረጋገጥ የቻሉት በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ላይ በመስራታቸው ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኢኮኖሚውን የሚደግፉና ሀገር ገንቢ ትውልድ የሚያፈሩ በመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና ትብብር በማድረግ ተቋማቱን የማጠናከር ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ተስፋሁን መኮንን በበኩላቸው አዲሱ ፖሊሲና ስትራቴጂ ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ለትምህርትና ስልጠና ጥራት መረጋገጥ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለተግባር ልምምድ ልዩ ትኩረት የሰጠና አለም አቀፍ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መንገድ በገበያ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
ኮሌጁ በየዓመቱ ከሶስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ገበያ ተኮር በሆኑ የሙያ መስኮች አሰልጥኖ በማብቃት አምራች ኢንዱስትሪውን እየደገፈ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ለአራት ቀናት በሚቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይም የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከጎንደር ከተማ፣ ከማእከላዊና ከሰሜን ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ የመንግስትና የግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲኖች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡