ቀጥታ፡

አስተዳደሩ ዲጂታል ማንነትን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የተሟላ ሥርዓት እየዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዲጂታል ማንነትን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥ የሚያስችል የተሟላ ሥርዓት እየዘረጋ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትግበራን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፤ ዲጂታል 2030 ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን መገንባት ቁልፍ የስትራቴጂው ግቦች እንደሆኑ አስረድተዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ የሚሰጣቸው የመንግስት አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በፈጠረው መደላድልም ተቋማትን የማገናኝትና እንዲናበቡ የማድረግ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማዘጋጀትም የተገልጋዩን የአገልግሎት እርካታ ማሳደግ የሚያስችል አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

በመሆኑም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በመዲናዋ በሁሉም ተቋማት ዲጂታል ማንነትን ማሰረት ያደረጉ አገልግሎቶች የሚሰጡበት የተሟላ ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከተማ አስተዳደሩ ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አኳያ ራሱን በመቃኘት የነዋሪዎችን የዲጂታል መታወቂያ መረጃን የማዋሀድ ስራ እንደሚሰራም ነው የጠቀሱት።

በመዲናዋ የተለያዩ ተቋማት በሚሰጡ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች ነዋሪው ባለበት ሆኖ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የገለጹት።

በዋናነትም የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎትም ከፋይዳ መታወቂያ ጋር እንዲያያዝ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት መደላድል መፈጠሩን አብራርተዋል።

የስማርት ሲቲ መገለጫ ዲጂታል አገልግሎትን በተሟላ መልኩ መስጠት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የነዋሪነትና የሲቪል ምዝገባ ስርዓቱ ፍትሐዊ፣ ተጠያቂነት ያለበት፣ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ የፋይዳ መታወቂያ እንዲይዙ ይደረጋል ነው ያሉት።

የሚሰጡ አገልግሎቶች ዲጂታል እንዲሆኑ መደረጉ ብልሹ አሰራርን ለማስቀረትና ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም