ቀጥታ፡

በክልሉ የመማር ማስተማር ስራ ቅድሚያ የሚሰጠው ቁልፍ የልማት ተግባር ሆኖ ይቀጥላል -ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና ተደራሽነትን ማስፋት ቅድሚያ የሚሰጠው ቁልፍ የልማት ተግባር ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ የትምህርት ዘርፉ ከልማቶች ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው የዘላቂ እድገት አቅም ነው።

በመሆኑም በክልሉ የመማር ማስተማር ስራው ቅድሚያ የሚሰጠው ቁልፍ የልማት ተግባር ሆኖ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በክልሉ የተስተዋለው የሰላም መታጣት ችግር በመማር መስተማር ስራው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰው፤ ችግሩን በመቋቋም የተሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁንም የመማር ማስተማር ስራውንም ሆነ ሌሎች የልማት ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰላምን በዘላቂነት የማስፈኑ ስራ በተጀመረው አግባብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ግብዓቶችን በማሟላት፣ ከደረጃ በታች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና መሰል ለትምህርት ጥራት እንዲሁም ተደራሽነት የሚያግዙ ተግባራት ከየትኛውም ልማት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይከናወናሉ ብለዋል።

የትምህርት ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ትብብር በማድረግ የትምህርት ተቋማትን በባለቤትነት በመገንባትና ግብዓት በማሟላት የሚጠበቅበትን ሚና ሁሉ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የትምህርት ቤት ምገባ ለትምህርት ሽፋን ማደግና ጥራት መረጋገጥ እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁንም የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ከመንግስት ባለፈ ባለሃብቱና ማህበረሰቡ በንቅናቄ ሊሰራው ይገባል ብለዋል።


 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ በበኩላቸው፤ ለመማር መስተማር ስራው የሚያግዙ ግብዓቶችን በተቻለ አቅም ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ተደራሽነትን ለማረጋገጥም የ63 ትምህርት ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡን በማስተባበር በራሱ አቅም ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት እንዲያበቃ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በአሰራር የሚስተዋሉ ክፍተቶችንና የግብዓት አለመሟላትን በጥናት ላይ መሰረት ያደረገ ምላሽ ለመስጠትም ቡድን ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ የክልሉን የ5 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ከገመገመ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጡም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም