አካል ጉዳተኞችን በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
አካል ጉዳተኞችን በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡- አካል ጉዳተኞችን በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ የክህሎት አቅማችውን እንዲያሳድጉ ትኩረት መደረጉን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ገለጹ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና ልማት ማዕከል ጋር በመተባበር የአካል ጉዳተኞች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የአካቶ መመሪያ የትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ስምኦን (ዶ/ር) ፤ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ አካል ጉዳተኛ ወገኖች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከመጥቀም ባለፈ ሀገራቸውን እያገለገሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በአካል ጉዳተኞች የሚመሩ ግዙፍ ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ወገኞች በክህሎት ልማት ማብቃት ከተቻለ የበለጠ ምርታማ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አካል ጉዳተኞችን በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ሀገር አቀፍ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰዋል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ በተዘጋጀው የአካል ጉዳተኞች የአካቶ ትምህርት መመሪያ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመምከር መሆኑን አመላክተዋል።
አዲሱ መመሪያ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የአካቶ ትምህርት ተደራሽነትን፣ ክብር ያለው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትንና ምቹ የስራ ቦታ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
መመሪያው በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ስምኦን(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በተለይም አካል ጉዳተኞችን በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የተሰራው ስራ በርካታ ወገኖችን ስኬታማ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲሱ መመሪያም አካል ጉዳተኞች በእውቀት ላይ የተመሠረተ ተግባር እንዲያከናውኑ በማድረግ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።