ቀጥታ፡

የሻሸመኔ ከተማ የኮሪደርና የመንገድ መሰረተ ልማት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴን ለማፋጠን አግዟል-ነዋሪዎች

ሻሸመኔ፤ታህሳስ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የሻሸመኔ ከተማ የኮሪደርና የመንገድ መሰረተ ልማት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ለማፋጠን ማገዙን ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማዋ ከ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ከ26 ኪሎ ሜትር በላይ የተቀናጀ የኮሪደር ልማትና የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑም ተመላክቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ በኢትዮጵያ ከተሞች ጽዱ፣ ለኑሮ ምቹና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ታስቦ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በተለያዩ ከተሞች እየተተገበረ ነው።

ልማቱ ተግባራዊ ከሆነባቸው የሀገራችን ከተሞች አንዷ ሻሸመኔ ስትሆን በአስተዳደሩና በነዋሪው ትብብር እየተከናወነ ባለው የተቀናጀ የኮሪደርና የመንገድ መሰረተ ልማትም ከተማዋ እየደመቀች ነው።


 

የልማት ሥራው የነዋሪውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ የከተማዋን ዕድገት ከማፋጠን ባለፈ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ከድር ገለቶ፣ ወይዘሮ በሻዬ ኤዶ እና አቶ ከድር አማን እንዳሉት፥ በከተማዋ የሚከናወኑት የልማት ስራዎች አዝጋሚ የነበረውን የከተማዋ እድገት የቀየሩና የነዋሪውን የልማት ጥያቄዎች የመለሱ ናቸው።

በተለይ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ለስራ ተመራጭ እያደረጋት መምጣቱን ገልጸዋል።


 

የኮሪደር ልማቱ ምቹ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገዶች ማካተቱ የትራፊክ መጨናነቅን እያስቀረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የከተማዋ ልማት ካላት ሰላም ጋር ተዳምሮ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲፋጠኑ በማድረጉ ለሥራ ዕድል ማገዙንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በኮሪደር ልማቱ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል አቶ ደጀኔ ስሜ ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ ከ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ከ26 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማትና የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ ነው ያሉት ደግሞ የአስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲሳ ገመቹ ናቸው።


 

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ አጠቃላይ የከተማዋ የመሰረተ ልማት ሥራ ውበትና ገጽታን ከመቀየር ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማፋጠን የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት እያሳደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በከተማዋ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን በማስፋት ከተማዋን ተመራጭ፣ ተወዳዳሪና ምቹ የማድረግ ሥራው ይጠናከራል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የህዝብን የልማት ተሳትፎ በማጠናከር እስከ መጪው ግንቦት ወር ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አዳነ ተክለጊዮርጊስ በበኩላቸው፥ በከተማዋ ከዚህ ቀደም የነበረው የመንገድ ዝርጋታ ለሰውና ለተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ምቹ እንዳልነበር አንስተዋል።


 

አሁን እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትና የአስፓልት መንገድ ግንባታ እነዚህን ችግሮች ከመፍታት ባለፈ ከተማዋን ዘመናዊና ተመራጭ በማድረግ የነዋሪውን ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብለዋል።

በከተማዋ ኮሪደርን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉት መሰረተ ልማቶች ሲጠናቀቁ በነዋሪው ህይወት ላይ ከፍተኛ መሻሻል እንደሚያመጡ የጠቀሱት ከንቲባው፣ ልማቱ በተያዘው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅም ልዩ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ስኬታማነት በሀሳብና በተግባር እያደረጉት ላለው ያላሰለሰ ትብብርና ድጋፍም ከንቲባው አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም