ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው
ሀዋሳ ፤ ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፡ በክልሉ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።
በዚህም ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ቡና አጥበውና ፈልፍለው ከሚያዘጋጁ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር የቡና ጥራትንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኢንዱስትሪዎች ጋር የተፈጠረውን ትስስር ከቡና ጥራት ባሻገር አርሶ አደሩ ከምርቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ እያስቻለ መሆኑን ጠቁመው ባለፈው ዓመት 10 ኢንዱስትሪዎች ትርፍ ክፍፍል ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በንሳ ወረዳ ትስስር ከፈጠሩ አርሶ አደሮች ቡና የሚረከቡ ባለሃብቶች ፤ ትስስሩ ጥራትንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም አርሶ አደሩ ከችግኝ ተከላ እስከ ቡና ለቀማ የባለሙያ ድጋፍ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ለኢንዱሰትሪዎች ቡና ከሚያቀርቡ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አስፋው ሆሼ፤ ከተከላ ጀምሮ እስከ ቡና ለቀማ የባለሙያዎችን ምክር ተቀብለው በመስራታቸው የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከደረሰ ማሳቸው የለቀሙትን ከ220 ኪሎ ግራም በላይ ቡና ትስስር ለፈጠሩት ኢንዱስትሪ በማቅረብ በተገቢው ዋጋ መሸጣቸውን ተናግረዋል፡፡