በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ስራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ስራ ገብተዋል
ሚዛን አማን፤ ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ከ2 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትልና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ከመሆኑም ባሻገር ምቹና ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም ያለው ነው።
ባለፉት አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ2 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
ፈቃድ አግኝተው ወደ ሥራ ከገቡ 42 ባለሀብቶች መካከል 34ቱ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን ይህም ክልሉ ለግብርና ሥራ ምርታማነት ያለውን ምቹ አጋጣሚ ወደ አኮኖሚ ለመቀየር የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
በተፈጠረው ኢንቨስትመንትም ከ6 ሺህ 700 ሔክታር በላይ መሬት የሚለማ ሲሆን በዚህም 36 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።
ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የክልሉ መንግሥት እያከናወነ ባለው የንቅናቄ ሥራ ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታን የመፍጠርና ሌሎች የማበረታቻ ድጋፎችን የማድረግ ተግባራት እንደሚጠናከሩም አክለዋል።
በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በግብርና ዘርፍ የተሰማራው ዳዊት የተቀናጀ የእርሻ ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክሉ አደራ፤ ምርጥ የፍራፍሬ ምርቶችን እና አትክልቶችን በብዛት የማምረት ተግባር ውስጥ ገብተው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉ ባመቻቸው የኢንቨስትመንት ዕድል ቦታ ወስደው የተሻሻሉ ዝርያዎችን በአካባቢው በማላመድ በመስኖ ጭምር ማልማት የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው የዘርፉን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድጉም ገልጸዋል።
በኢንቨስትመንቱ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት ጌታቸው አሊ፤ በእርሻ ልማቱ በሚያከናውነው ሥራ ገቢ በማግኘት ራሱን ከማስተዳደር ባሻገር ውጤታማ የግብርና ሥራ ልምድ በማግኘት የራሱን አቅም የማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረለት አክሏል።