ቀጥታ፡

የተሟላ መሰረተ ልማት ያላቸው የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ የግብርና ምርቶችን የገበያ ተደራሽነት ማስፋት የሚያስችሉ የተሟላ መሰረተ ልማት ያላቸው የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግል አልሚዎችን ያሳተፈ የኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት የጎላ አበርክቶ እየተወጣ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን የገበያ ተደራሽነት ለማስፋት አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር ሶስት የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መጠናቀቁን ገልጸው፤ የነቀምትና ማዕከላዊ ጎንደር የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተጀምሯል ብለዋል፡፡


 

የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የግሉን አምራች ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ይሄውም በፓርኮቹ የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ውጤቶች ለውጭ ንግድ እና የሀገር ውስጥ ገበያን ለማረጋጋት የጎላ አበርክቶ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተቀናጀ ድጋፍና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ አዋጭነቱ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለግሉ ባለሀብት የተመቸ የኢንቨስትመንት ከባቢ እየፈጠረች መሆኑን ጠቅሰው፤ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጓቸው ምርቶችን ለማምረት በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም