ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በአገልግሎት አሰጣጥና በዜጎች አኗኗር ላይ መሰረታዊ ለውጥ አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በአገልግሎት አሰጣጥና በዜጎች አኗኗር ላይ መሰረታዊ ለውጥ አምጥቷል
አርባምንጭ ፤ ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡-የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በአገልግሎት አሰጣጥና በዜጎች አኗኗር ላይ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ መሆኑን በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በስኬት መጠናቀቁንና የ2030 ትግበራ በይፋ መጀመርን ማብሰራቸው ይታወቃል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ትልቅ ስኬት የተመዘገበ መሆኑን በማንሳት በቀጣይ ደግሞ ተደራሽነትን የማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል የመፍጠር እና በዜጎችና በተቋማት መካከል ይበልጥ መተማመንን የማጎልበት ጉዳይ ትኩረት የሚደረግበት መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ የሃይል እና የኢንተርኔት ተደራሽነትን በማስፋት ለተግባራዊነቱ መትጋት ይገባል ብለዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በአገልግሎት አሰጣጥና በዜጎች አኗኗር ላይ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒቲንግና ሶፍትዌር ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና የኤሌክትሮኒክ ትምህርት አስተዳደር ክፍል ዳይሬክተር መሐመድ አበበ (ዶ/ር)፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት በዜጎች አኗኗር ላይ በተግባር የተገለጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገሪቱን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ካሻገሩ አንኳር ተግባራት መካከል አንዱ የግብይት ስርአቱ ዲጂታላይዝድ መሆን እንደሆነ አንስተው የመንግስት ግዥም በአብዛኛው ዲጂታል መሆኑ ብዙ ውስብስብ ችግሮችን ስለመፍታቱ አብራርተዋል።
መንግስት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለመቆጣጠር ብሎም አገልግሎትን ለማሳለጥ የዘረጋው የፋይዳ መታወቂያ ስርአትም ዜጎችን በብዙ መልክ ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።
በድመሩ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሚታይ ለውጥና የሚቆጠር ውጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸው የ2030 ስትራቴጂን በላቀ ስኬት ለመከወን የሁላችንም እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የመረጃ ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር መምህር ኢያሱ ዲላ (ዶ/ር)፤ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬት መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዞ በመስራቱ የሚፈለገው ውጤት መጥቷል ብለዋል።
በቴክኖሎጂ ታግዞ የተጀመረው መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ማግኘት ያስቻለ ዘመናዊ አሰራር መሆኑን አንስተው የኮደርስ ስልጠና፣ የባንክ አገልግሎቶች፣ የግብር ክፍያና ሌሎችም መንግስታዊ አገልግሎቶች የ2025 ስትራቴጂ ስኬት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ከቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ መደረጉ ይታወቃል።