የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሀገርን ሁለንተናዊ ልማትና እድገትን ለማሳካት ጠንካራ መሰረት አኑሯል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሀገርን ሁለንተናዊ ልማትና እድገትን ለማሳካት ጠንካራ መሰረት አኑሯል
መቀሌ፤ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሀገርን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ለማሳካት ጠንካራ መሰረት ያኖረ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠናቂቂያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የማስመጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ የተሳካ መሆኑን ገልጸዋል።
በስትራቴጂው በግብርና፣ በማዕድን ብሎም በኢንዱስትሪው እንደተገኘው ስኬት በዲጂታሉ ዘርፍም መገኘቱን አንስተው፥ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት ፅኑ መሰረት እንደሚሆነው አመላክተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በትግራይ ክልል የሚሰሩ የዘርፉ ባለሙያዎች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሀገርን ሁለንተናዊ ልማትና እድገትን ለማሳካት ጠንካራ መሰረት ያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
የሽግግር ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ባለሙያና ተመራማሪ የሆኑት ኢንጂነር ፍሰሃ ነጋ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አተገባበርና የተገኘው ስኬት አስደናቂ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህም በመነሳት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግና ማሳካት የሚቻል መሆኑን ገልጸው፥ የዲጅታል አገልግሎትን ማስፋት ሀገራዊ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የአይ ሲ ቲ ባለሙያዋ ወጣት ራሄል ገብረ ፃድቅ በበኩሏ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የዜጎችን የአኗኗር ሁኔታ በፍጥነት የቀየረና ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ገልፃለች።
የዲጂታል አገልግሎት ከአገልግሎት ጥራትና ፍጥነትም ባለፈ የተገልጋዮችን እንግልት የሚያስቀርና የሀገርን ሃብት ከምዝበራ ለመታደግ የሚያስችል መሆኑን አንስታለች።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የልማት ይዘቶች ባለሙያ ዳንኤል ገብረመስቀል፤ የመሬትን ጨምሮ የሃገር ሃብትን ለመቆጣጠርና ሌብነትን ለመከላከል የዲጂታል አሰራር ስርዓት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የዲጂታላይዜሽን አገልግሎት የአሰራር ፍጥነትን፣ ቁጥጥርንና ተጠያቂነትን ጭምር እውን በማድረግ ለዜጎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ቁልፍ ትልሞች ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና በተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት መሆኑም ይታወቃል።