ኢትዮጵያ የምርት ገበያ ልምዷን ለአፍሪካ ሀገራት በማካፈል አህጉራዊ ሚናዋን እየተወጣች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምርት ገበያ ልምዷን ለአፍሪካ ሀገራት በማካፈል አህጉራዊ ሚናዋን እየተወጣች ነው
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በምርት ገበያ አሠራር ሥርዓት ያካበተችውን ሰፊ ልምድ ለአፍሪካ ሀገራት በማካፈል አህጉራዊ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የፈጠረው ዐቅም የአፍሪካ ሀገራት ልምድ የሚቀስሙበት አህጉራዊ ተቋም መሆን እንዳስቻለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መርጊያ ባይሳ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ተቋሙ ጥራትን የግብይት ዋነኛ መለኪያ በማድረግ ረገድ ትልቅ ስኬት ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ ለ28 የምርት ዓይነቶች ዝርዝር የጥራት መመዘኛ መስፈርቶች ወጥቶላቸው ግብይት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አካዳሚ ተቋቁሞ በቡና ቅምሻ፣ በጥራጥሬና በቅባት እህሎች ምርመራ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሰልጣኞች እየተሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።
ተቋሙ የሚከተለው የተቀናጀ የአሠራር ሞዴል አርአያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ታንዛኒያ፣ አንጎላና ጋና የኢትዮጵያን የቢዝነስ ሞዴልና የጥራት ቁጥጥር ሥርዓት መነሻ አድርገው የራሳቸውን ምርት ገበያ መስርተዋል ብለዋል።
በቅርቡ ከታንዛኒያና ኬንያ የመጡ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ሥልጠና መውሰዳቸውን እንዲሁም የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ወደ ሌሎች ሀገራት በማቅናት ድጋፍና ሥልጠና እየሰጡ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የአካዳሚውን ዐቅምና መሰረተ ልማት በማሳደግ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።