ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በመደመር መርህ ያስመዘገቡት ስኬት ነው

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በመደመር መርህ ያስመዘገቡት ታላቅ የልማት ስኬት መሆኑን የቤንሻንጉል ጉሙዝ  ክልል ርዕሰ መስተዳድር  አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተዘጋጀው ''ስለ ኢትዮጵያ'' የውይይት  መድረክ  ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሚገኝበት ጉባ ''ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት'' በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።  


 

በመድረኩ የህዝብ  ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ  የመንግሥት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ  የተለያዩ  ባለድርሻ  አካላት ተገኝተዋል። 

የቤንሻንጉል ጉሙዝ  ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በውይይቱ መክፈቻ እንዳሉት፣ኢትዮጵያዊያን የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን ተቋቁመው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን አሳክተዋል። 

ይህም ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆም የሚፈለገውን ውጤት እንደሚያመጣ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግድቡ ለክልሉ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠሩንም ነው ያነሱት።

በግድቡ ምክንያት የተፈጠረው ንጋት ሀይቅ ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በመደመር መርህ ያስመዘገቡት ታላቅ የልማት ስኬት ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤  ግድቡ ለኢንዱስትሪ  ልማት ፣በሃይል አቅርቦት ቱሪዝምና የወል ትርክት ግንባታ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም