ቀጥታ፡

ከ706 ሺህ 306 ሔክታር በሚልቅ ማሳ ላይ የለማ የቅመማቅመም ሰብል እየተሰበሰበ ነው

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡-በተያዘው ዓመት ከ706 ሺህ 306 ሔክታር በሚልቅ ማሳ ላይ የለማ የደረሰ የቅመማቅመም ሰብል እየተሰበሰበ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

በባለሥልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዘንድሮ ከ12 በላይ ዋና ዋና የቅመማቅመም ዓይነቶች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየለሙ ይገኛሉ።


 

እነዚህን የቅመማቅመሞች ዓይነቶች ለማዘመን፣ ምርታማነትንም ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት የተሻሻሉ ዝርያዎችን ከመልቀቅ፣ባህላዊ አስተራረስና ምርት አሰባሰብን ከማዘመን ጀምሮ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በሌላ በኩል ከዘር ብዜትና አቅርቦት ጋር ውስንነት እንደሚስተዋል ጠቅሰው፤ ይህን ለማስተካከል ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በከፍተኛ ደረጃ እየለሙ እና እየተሰበሰቡ ካሉት ዋና ዋና የቅመማቅመም ዓይነቶች መካከልም፤ ጥቁር አዝሙድ፣ ነጭ አዝሙድ፣ አብሽ፣ ድንብላል፣ ዝንጅብል፣ ዕርድ፣ በርበሬ፣ ቫኒላ፣ ኮረሪማ፣ ሮዝመሪ እና ሌሎችም ይገኙበታል ብለዋል።

እስካሁን እየለሙ የሚገኙ የቅመማቅመም ዓይነቶች አማካይ ምርታማነት በሔክታር 18 ነጥብ 5 ኩንታል መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም