ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። 

በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 7 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከምድረገነት ሽሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች በአራቱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።  ቡድኑ በ17 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ምድረገነት ሽሬ  ከ10 የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 

ምድረገነት ሽሬ በ14 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  ሁለቱም ክለቦች በሊጉ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች አምስቱን ሲያሸንፍ በአራቱ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ በ16 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ እስከ አሁን ማሸነፍ የቻላቸው ጨዋታዎች ብዛት ሁለት ብቻ ናቸው። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ በአምስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።

የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ11 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

ሸገር ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 10 ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ በ12 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። 

በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 10 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ያሸነፈው ሃዋሳ ከተማ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ሃዋሳ ከተማ በ17 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ኢትዮጵያ ቡና በ12 ነጥብ 14ኛ፣ ድሬዳዋ ከተማ በ13 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዘዋል። ጨዋታዎቹ በዋንጫ ፉክክሩ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም