ኢትዮጵያ ጠንካራ እና አካታች የጤና ስርዓት ለመገንባት እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ ነው-የዓለም ጤና ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ጠንካራ እና አካታች የጤና ስርዓት ለመገንባት እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ ነው-የዓለም ጤና ድርጅት
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 16/2018(ኢዜአ)፦የዓለም የጤና ድርጅት ኢትዮጵያ አይበገሬ እና ሁሉን አካታች አካታች የጤና ስርዓት ለመገባት እያከናወነች ያለውን ስራ የሚደነቅ መሆኑን ገለጸ።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክቷል።
በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና ምላሽ ቡድን መሪ ፓትሪክ ኦክሙ አቦክ፥ ኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመገንባት እና የአደጋ ተጋላጭ ማህበረሰብ ክፍሎች ጥበቃ ላይ እያከናወነች ያለውን ስራ የሚደነቅ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ቡድን መሪው ኢትዮጵያ የስደተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፥በክትባት ፕሮግራሞች እና በማህበረሰብ ጤና ኢኒሼቲቮች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አንስተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በቅርበት እየሰራ ነው ብለዋል።
ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለሁሉም ዜጋ እኩል ተደራሽነትን የሚፈጥር ጠንካራ እና አካታች የጤና ስርዓት እንዲገነባ በአጋርነት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
አንድም ህጻን ሳይከተብ መቅረት የለበትም በሚል እሳቤ የዓለም የጤና ድርጅት በክትባት ዘመቻዎች ላይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ በጤና ክብካቤ፣የህክምና መሳሪያዎች እና ግብአቶች በማቅረብ፣ የአደጋ ጊዜ ምላሽ እንዲሁም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ መንግስት የጤና መሰረተ ልማቶችን ደረጃ በማሻሻል እና በገጠርና አስቸኳይ ድጋፍ በሚያስፈልግባቸው ቦታዎች የጤና አገልግሎትን ባልተቋረጠ ሁኔታ መስጠቱ የሚደነቅ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።
አቦክ ኢትዮጵያ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች እና በየአካባቢው ያሉ የመንግስት መዋቅሮች አማካኝነት በማህበረሰብ ጤና ፕሮግራም የአይበገሬነት አቅም ለመገንባት እያከናወነች ያለውን ስራም አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ እና የዓለም የጤና ድርጅት በትብብር መስራት የጀመሩት እ.አ.አ በ1951 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።