መንግሥት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ታኅሣስ 15/2018(ኢዜአ)፡-መንግሥት የሀገር ግንባታ ሂደቱን ለማጽናት እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ዲሞክራሲን መገንባት፣ ተቋማትን ማጠናከርና ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን ገልጿል፡፡
እነዚህ ሦስቱ ምሰሶዎች ሀገራዊ አንድነትን፣ሰላምና ብልጽግናን፣ እንዲሁም ዜጎች በመተማመን እና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ የጋራ ራዕይ እንዲኖራቸዉ የሚያደርጉ ቁልፍ መሰረቶች ናቸው፡፡
ዲሞክራሲን የመገንባት ሂደት ለአንድ ሀገር ወሳኝ ተግባር ሲሆን፣ በዋናነት ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቁ ተቋማትን ማቋቋም ላይ ትኩረት ያደረገ ነዉ፡፡ተቋማቱ የሚመሩባቸዉ ህጎችና የአሰራር ሥርዓቶች፣የተቋማቱ አወቃቀርና አደረጃጀት፣ እንዲሁም ለህዝብ ያላቸዉን ተዓማኒነትን መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራበት ይገኛል፡፡
ጠንካራ የዲሞክራሲ ባህልና ሥርዓት የሚገነባው ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት ሲፈጠሩና ሲጠናከሩ መሆኑን መንግሥት በጽኑ የሚገነዘበው ጉዳይ ነዉ፡፡በዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት 7 ዓመታት በዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሂደት ውስጥ ሁለተናዊ ሪፎርም ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች፡፡
እነዚህ ሪፎርሞች የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑትን የዲሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ እና ጠንካራ አድርጎ ለመገንባት መንግሥት ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ ያሳየባቸው ናቸው፡፡
የእነዚህ ተቋማት መጠናከር በአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላም እና ልማት እንዲረጋገጥ እንደ ዋንኛ ምሰሶ የሚወሰድ ነው፡፡
በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በዲሞክራሲ ተቋማት ላይ የታዩ ተጨባጭ ለውጦች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለመጠበቅ፣ እንዲሁም የሕዝቡን ዕምነት ለማጠናከር ወሳኝ እርምጃ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ መንግሥት በተለይ ተቋማዊ ዐቅምን በማሳደግ እና ነፃነትን በማረጋገጥ፣ የዲሞክራሲ ምህዳርን እንዲሰፋ ለማደረግ የሚጠበቅበት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲ የሚያብብበትን አስቻይ ዐውድና ማዕቀፍ ለመፍጠር ዓለማው አድረጓል፡፡
ይሄንን ከግብ ለማድረስ በተለይ የፀጥታ፣ የፍትሕ፣ የሲቪልና የሚዲያ ተቋማት፣ እንዲሁም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝብን ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ መንግሥት በቁርጠኝነት በመደገፉ እንደ ሀገር ገለልተኛ ተቋማት እንዲፈጠሩ በማደርረግ ተጨባጭ ዉጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል፡፡
ሌላው መንግስት በትኩረት እየሰራበት ያለው ጉዳይ እንደ ሀገር ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ነዉ፡፡
ይህ ሂደት ዋና ዓለማ ያደረገው መላዉ ሕዝብ፣ ተቋማት፣ አመራርና ሠራተኛዉ በሀገራዊ ራዕይ ላይ በተለያዩ ድምጾች የጋራ እድገትን በመገንባት ሀገራዊ ህለውና እና ብልጽግና እንዲረጋገጥ እንዲሁም በዜጎች መካከል መተማመን እና ሀገራዊ አንድነትን እንዲፈጠር ማድርግ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የብዙሃን ድምጽ የሚሰማበት የፖለቲካ ዐዉድ ለመፍጠር አያሌ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን አድርጋለች፡፡
በዚህም እስከዛሬ በነበሩ መንግሥታት ያለተሞከረውን ጫፍ ወጥተው የሚታዩ ተቃርኖ ሀሳቦችን ለማጥበብና ለማቀራረብ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም፣ ሀገራዊ የውይይት መድረክ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡
በዚህም ገና ከወዲሁ በርካታ ለዉጦች እየታዩ ሲሆን ውሳኔው ለምንመኛት የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን መሆን የማዕዘን ድንጋይ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
በአጠቃላይ መንግሥት መልአተ ሕዝቡን በማስተባበር ጠንካራና ብልጽግናዋን በልጆቿ ያረጋገጠች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እያደረገ ባለው ዘርፈ ብዙ ጥረት ዲሞክራሲን መገንባት፣ ተቋማትን ማጠናከርና ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠርን ጉዳይ በልዩ ትኩረት የሚሰራበት ዋንኛው አጀንዳው ሆኖ ይቀጠላል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት